Fana: At a Speed of Life!

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ከነ ቀኖናዋ፣ ከነ ትውፊቷና ማንነቷ ለትውልድ እንድትሸጋገር በታማኝነት አገልግለዋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የሚያምኑትን አምላክ እና የሚወዷትን ቤተክርስቲያን በታማኝነት ያገለገሉ አባት ናቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አስክሬን የሽኝት መርሃ ግብር በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፣ብፁዓን አባቶች እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ነው የሽኝጽ መርኃ ግብሩ የተካሄደው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሽኝት መርሃ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “አባታችን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ እንደ ጥሩ አባት ሩጫቸውን ጨርሰው ወደ ሚወዱት አባታቸው ሄደዋል” ብለዋል፡፡

“አባታችን እድለኛ ናቸው፤ እድሜያቸውን በሙሉ የሚወዷት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን በታማኝነት አገልግለዋል” ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ብፁዕነታቸው መናገር ሲገባቸው ተናግረው፤ መጸለይ ሲገባቸው ጸልየው፤ መምከር ሲገባቸው መክረው ፤ በአርምሞ እና በጸጥታ መኖር ሲገባቸው እንዲሁ አድርገው በብዙ ያስተማሩን አባት ናቸውም ብለዋል፡፡

“አባታችን ፈታኝ ነገር ሲገጥመን በጸሎት እና በምክር ያግዙኝ ነበር” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ሃሳባቸውንም በጹሑፍ በተደጋጋሚ ልከውልኛል ብለዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ለ26 ዓመታት ተለያይቶ የነበረውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አንድ እንዲሆን ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

“ከአባታችን ልንማር የሚገባን ኦርቶዶክስ ከነ ቀኖናዋ፣ ከነ ትውፊቷ እና ማንነቷ ወደ ትውልድ እንድትሸጋገር ከግጭት እርስ በርስ ከመሰዳደብ ወጥተን በመተባበር መንፈስ አብረን መስራት እንዳለብን ነው” ሲሉም መክረዋል፡፡

አሁን ወቅቱ የጸሎት ጊዜ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ምዕመናን ለአገራቸው ኢትዮጵያ ሰላም እና ለአባታችን እረፍት እንዲጸልዩም ጠይቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመርሃ ግብሩ ላይ የስንብት አበባ ጉንጉን ያስቀመጡ ሲሆን፥ በብጹዕነታቸው እረፍት የተሰማቸውን ሃዘንም በክብር መዝገብ ላይ አስፍረዋል።

በመላኩ ገድፍ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.