ክሳቸው ከተቋረጠላቸው መካከል ከሜቴክና ከሰኔ 15ቱ ክስተት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ይገኙበታል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከዚህ ቀደም በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው የነበሩ 63 ተጠርጣሪዎች ክሳቸው እንዲቋረጥ መደረጉን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ፀጋ እና የመስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ከዚህ ቀደም በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው በክስ ሂደት ላይ የነበሩ 63 ተጠርጣሪዎች ክሳቸው እንዲቋረጥ መደረጉን አስታውቀዋል።
ክሳቸው ከተቋረጠው በትናንትናው እለት በመንግስት ከተገለፀው 60 ግለሰቦች ላይ በዛሬው እለት 3 ግለሰቦችን በመጨመር በአጠቃላይ የ63 ተጠርጣሪዎች ክስ መቋረጡን ነው የገለፁት።
ክሳቸው ከተቋረጠላቸው ግለሰቦች መካከልም ከሜቴክ፣ ከሶማሌ ክልል፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ከሲዳማ እንዲሁም ከሰኔ 15 ኩነት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ውለው የክስ ሂደት ላይ የነበሩ እንደሚገኙበትም አብራርተዋል።
በዚህም በሜቴክ ውስጥ ከተፈፀመ ሙስና ጋር ተያይዞ ከተከሰሱት ውስጥ የተወሰኑት ተጠርጣሪዎች ክስ እንዲቋረጥ መደረጉን እና ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘም ክሳቸው የተቋረጠላቸው የአመራርነት ሚና ያልነበራቸው እንደሆኑም አስታውቀዋል።
ለሀገራዊ አንድነት እና ለለውጡ የሚኖረው ፋይዳን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ለህዝብ እና ለሀገር ጥቅም ሲባል እንዲሁም የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል።
በመግለጫው በማከልም በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ከተጠረጠሩ ከ3 ሺህ 606 ግለሰቦች ውስጥ እስካሁን 1 ሺህ 682 የሚሆኑት ብቻ በቁጥጥር ስር ውለው የክስ ሂደት እየተካሄደ መሆኑም ተገልጿል።
በቀጣይ ጊዜም በቁጥጥር ስር ያልዋሉትን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በቁጥጥር ስር ውለው ለህግ እንዲቀርቡ የማድረግ ስራ ይሰራል ተብሏል።
ከዚህ በኋላም በማህበራዊ ሚዲያም ይሆን በሌሎች አግባብ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ የጥላቻ ንግግር የሚነዙ አካላት ላይ በቅርቡ በፀደቀው አዋጅ መሰረት ቁጥጥር እንደሚደረግ እና አጥፊዎችም ለህግ እንዲቀርቡ እንደሚደረግም ነው የተገለፀው።
ከሙስና ጋር በተያያዘም ጠቅላይ አቃቤ ህግ በቅርቡ ክትትል እያደረገ ያለ ሲሆን፥ አጥፊዎችን ለህግ የማቅረብ ስራም በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሰራል ብሏል።
በህገ ወጥ የጦር መሳሪያ እና በሌሎች የወንጀል ተግባራት ላይ ተሳትፈው የተገኙ አካላትንም በመለየት በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ እንደሚሰራም ነው በመግለጫው ያስታወቁት።