Fana: At a Speed of Life!

መንግስት ለትግራይ ህዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርስ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራሉ መንግስት ለትግራይ ህዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርስ አስፈላጊውን ገንቢ ሚና እየተጫወተና ዕርዳታ እንዲላክ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ ።
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ፥ መንግስት ለትግራይ ህዝብ አስፈላጊ የሆኑ የምግብና የመድሃኒት ድጋፎች በአፋር ክልል በኩል እንዲደርሱ ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠሩ በተጨማሪ በዛሬው ዕለት ብቻ የምግብ አቅርቦቶችን የያዙ 20 የጭነት ተሸከርካሪዎች እና የነዳጅ ታንከሮችን የያዙ ሦስት ተሽከርካሪዎች ከሰመራ ወደ መቀሌ መጓዛቸውን አስታውቋል።

በክልሉ ህዝብ መሰረታዊ ሰብዓዊ ድጋፎች ፈጥነው እንዲደርሱ ለማድረግ ከቅርብ ቀናት ጀምሮ በየዕለቱ 40 ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል እንዲጓጓዙ የሚደረግ መሆኑንም  ነው መንግስት ያስታወቀው።

መግለጫው እንዳመለከተው፥ ከትናንት ጀምሮ 17 ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያደርጉ አጋር ድርጅቶች ክትባትን ጨምሮ የተለያዩ መድሃኒቶች፣ የህክምና ቁሳቁስና የምግብ አቅርቦት ወደ ትግራይ  ክልል ማጓጓዝ እንደሚችሉ አረጋግጠዋል።

በዚህም መሰረት ሌሎች 11 አጋር ድርጅቶች  በጭነት አውሮፕላን 257 ሺህ 192 ኪሎ ግራም መድሃኒቶች፥ የህክምና ቁሳቁስና የምግብ አቅርቦቶችን ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ ማጓጓዛቸው ተገልጿል።

ከ700 ሺህ ህዝብ በላይ እንዲፈናቀል እና ከአብኣላ በኩል ወደ መቀሌ የሚደረገው የሰብዓዊ  አገልግሎት ጉዞ  እንዲቋረጥ ያደረገውም፥  በአፋር ክልል ላይ ዳግም ወረራ ያካሄደው  ሽብርተኛው የህወሓት ቡድን መሆኑ በግልጽ ሊታወቅ ይገባል ሲል መንግስት በመግለጫው አስገብዝቧል።

መንግስት የህዝቡን መብት ለማረጋገጥና በችግር ላይ ያሉትን ዜጎቹን ህይወት ለመታደግ  ከማንም በላይ ሃላፊነት እንደሚሰማው ገልጾ፥ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የሚላከው ሰብዓዊ  ድጋፍ ለህዝቡ በቀጥታ እንዲደርስ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስቧል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም  ችግሩን በሚመጥን ደረጃ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅበት አመልክቷል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.