Fana: At a Speed of Life!

በምግብ ራሳችንን ለመቻል ምርታማነታችንን ማፋጠን በእጅጉ ያስፈልገናል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የስንዴ አቅርቦት በዓለም አቀፍ ሁነቶች ጫና እየደረሰበት በመሆኑ በምግብ ራሳችንን ለመቻል ምርታማነታችንን ማፋጠን ይገባናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራ የሚኒስትሮችና የክልል ርእሰ መስተዳደሮች ልዑካን ቡድን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ዋዋ ቀበሌ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ጎብኝቷል፡፡

በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግብርና የሀገራችን የኢኮኖሚ መሠረት ሆኖ ቆይቷል፤ የስንዴ አቅርቦት በዓለም አቀፍ ሁነቶች ጫና እየደረሰበት በመሆኑ በምግብ ራሳችንን ለመቻል ምርታማነታችንን ማፋጠን በእጅጉ ያስፈልገናል ብለዋል።

ዛሬ በአማራ ክልል ያየነው ምርታማነት ተስፋ ሰጪ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የግብርና ጉዟችን አድካሚ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ተጋድሏችን የምርታማነታችንን መጠን በሚሊዮኖች ለማስፋፋት ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራሮች ከፓለቲካና ስብሰባ ጊዜ ቀንሰው ለኢኮኖሚው መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

ተስፋ ሰጪ የበጋ ሰንዴ ልማት እየተካሄደ መሆኑ በጉብኝቱ የተገለጸ ሲሆን÷ በአማራ ክልል 2 ሚሊየን ኩንታል የስንዴ ምርት እንደሚጠበቅም ተመላክቷል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግብርና ጉዞው አዝጋሚ በመሆኑ ዘርፉ በፍጥነት ሊመራ እንደሚገባ ገልጸው÷ በዚህም በምግብ ራስን መቻል እና አትርፈንም መሸጥ አለብን ብለዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና አርሶ አደሮች ለመስኖ ስንዴው መልማት ላደረጉት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በጉብኝቱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ እርስቱ ይርዳ፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሀመድ፣ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መለስ መኮንን እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

በምናለ አየነው

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.