Fana: At a Speed of Life!

በኮቪድ-19 እና በጸጥታ ችግር የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለማነቃቅት ያለመ ስልጠና በላሊበላ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኮሮና ወረርሽኝ እና እና በጸጥታ ችግር የተጎዱ ዋና ዋና የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማነቃቃት ያለመ እና የዘርፉን ተዋናዮች ያሳተፈ ስልጠና ላሊበላ ከተማ ተጀምሯል፡፡
 
ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የቱሪዝም ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ስለሺ ግርማ÷ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ መንፈሳዊ እና ማህበራዊ ጥቅም ትልቅ ዋጋ ያለውን የቱሪዝም ዘርፍ ላይ የኮቪድ-19 ስርጭትን ተከትሎ የተደረጉ የጉዞ እገዳዎች እና በአገሪቱ የተፈጠረው ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ማስከተላቸውን አስታውሰዋል፡፡
 
በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ቅርስ የሆኑት የላል ይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን እና ሌሎቹንም ቅርሶች መሰረት አድርገው የተፈጠሩት የሆቴል እና ቱሪዝም እንቅስቃሴዎችም ጉዳት እንደደረሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
 
ለቱሪዝም መዳረሻዎች መሰረተ ልማት መሟላት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አንዱ ዕቅድ መሆኑን መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
በሚኒስቴሩ የሰው ኃብት ልማት ዳይሬክተር አቶ በጋሻው ቅጣው በበኩላቸው ÷ በዚህ ወቅት የሥራ ዕድል ለመፍጠር የኢትዮጵያ ህልውና እና ትልቅ ተስፋ በሆነው የቱሪዝም ዘርፍ ላይ መወያየት እና በአስጎብኝነት እና በሆቴል ዘርፍ የተሰማራውን የሰው ኃይል ማነቃቃት እና ለአገልግሎቱ ዝግጁ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
 
ስልጠናውን የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በጋራ ያዘጋጁት መሆኑ ተመላክቷል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.