በጎንደር የተፈጠረው ችግር የኃይማኖት እሴትን የጣሰና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከቀናት በፊት በጎንደር ከተማ የተፈጠረ የሰላም መደፍረስ ችግር የኃይማኖት እሴትን የጣሰ እና ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለፀ።
ጉባኤው በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።
በከተማዋ በተፈጠረው ሁከት የሰው ህይወት ከማለፍ ጀምሮ የንብረት ውድመትና ዘረፋ ተፈፅሟል ብለዋል የጉባኤው ጠቅላይ ፀሃፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ።
የተፈጠረው ችግርም የኃይማኖት እሴትን የጣሰ እና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ነው አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩት።
ችግሩ እንዲቀረፍም በሰከነ መልኩ መነጋገር አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ፥ በዚህ አጋጣሚ ሀገርን ለማተራመስ እና ሌሎች ግጭቶችን ለመቀስቀስ እየተንቀሳቀሱ ያሉ አካላት ከተግባራቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል።
የኃይማኖት ተቋማት እና መሪዎችም ፍቅርና አብሮነትን በማስተማር ዜጎችንን ከዚህ ሁኔታ ውስጥ ሊያወጡ እንደሚገባም ነው የመከሩት።
ተሳታፊ የነበሩ አካላት ላይ መንግስት አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሳስቧል።
በአፈወርቅ አለሙ እና ተስፋየ ከበደ