Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ህብረት ተወካዮች የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደውን የሰላም ግንባታ እርምጃዎች አደነቁ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2014 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት አመታዊ የፖለቲካ ውይይታቸውን ዛሬ በአዲስ አበባ አካሂደዋል ።

ሁለቱ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት እና የአውሮፓ ህብረት እና የኢትዮጵያ ግንኙነትን በሚመለከት የተወሰዱ የሰብአዊ እና የተጠያቂነት እርምጃዎችን ጨምሮ የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የጋራ ተጠቃሚነትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜን ያለውን ግጭት ለማስቆምና የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ያሉ የተለያዩ እርምጃዎችን ዳሰሳ አቅርበዋል።

የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ በሰሜኑ ግጭት ወቅት በሁሉም አካላት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ጨምሮ መንግስት የወሰደውን የተጠያቂነት እርምጃ በተመለከተ መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ግብረ ሃይል በማዋቀር የጥሰት ተግባራትን ፣የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የጋራ ምርመራ እና ምክረ-ሀሳቦቹን ተግባራዊ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት እንዲሁም ወንጀለኞችን ወደ ህግ እንዲቀርቡ እየተሰራ ነዉ ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ÷ለትግራይ ክልል ያልተቋረጠ ሰብአዊ ድጋፍን ለማረጋገጥ እስካሁን የተወሰዱ እርምጃዎችን በቪዛ አሰጣጥ፣እርዳታ ሰጭዎች ወደ ትግራይ ይዘዉት የሚገቡት መጠን ፣ኬላዎችን በመቀነስ እና ሰብአዊነት ድጋፎች መጨመርን በመጥቀስ አብራርተዋል።

አቶ ምትኩ በኢትዮጵያ በድርቅና በግጭት ለተጎዱ ወገኖች ለሚደረገው ድጋፍ የሰብአዊ አጋሮች ምስጋናቸውን አቅርበው የአማራና አፋርን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የድጋፍ መሰረቱን ማስፋትና ለዘላቂ ልማትና መልሶ ማቋቋም ስራዎች ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል። .

በምክክር መድረኩ ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ክቡር አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ለሁለቱም ወገኖች አሁን ካጋጠሟቸው ፈታኝ ሁኔታዎች አንፃር ወቅታዊ መሆኑን ገልጸው በኢትዮጵያ ስላለው ግጭትና ድርቅ እንዲሁም በአውሮፓ የሩስያ እና የዩክሬን ግጭት አንስተዋል።

ውይይቱ ከሰብአዊ መብት ጥሰት እና ከተጠያቂነት እርምጃዎች በተጨማሪ በኢትዮጵያ ስላለው የንግድ ሁኔታ ከአውሮፓ ባለሃብቶች አንፃር የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት እና የዳበረ ኢኮኖሚ ለመገንባት ስለሚያስችለው ጉዳይ ተወያይተዋል።

የአውሮፓ ህብረት ተወካዮች የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደውን የሰላም ግንባታ ርምጃዎች እና በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለውን የድንበር ግጭት እና በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የተካሄደውን የሶስትዮሽ ድርድር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የገባውን ቃል አድንቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.