በለንደን የቡና አውደ ርዕይ ለማካሄድ የሚያስችል የምክክር መድረክ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በለንደን የቡና አውደ ርዕይ ለማካሄድ እና ከብሪታንያ ቡና ተረካቢዎች ጋር ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር የሚያስችል የምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡
በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተካሄደ የውይይት መድረክ÷ የኢትዮጵያን ቡና ቆልቶና ፈጭቶ ለብሪታንያ ገበያ ለማቅረብ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በቡና ዘርፍ ከተሰማሩ አካላት ጋር ነው ውይይቱ የተካሄደው፡፡
በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ አቶ በየነ ገብረመስቀል እንደገለጹት÷ እስከ አሁን ወደ ብሪታንያ ከኢትዮጵያ በቀጥታ እየተላከ ያለው ጥሬ ቡና መጠን ዝቅተኛ ነው፡፡
ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት መውጣቷን ተከትሎ ቡናን ቆልቶና ፈጭቶ ጥራት ባለው መንገድ በማቅረብ ወደ ገበያው በብዛት መግባት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
በወጪ የቡና ንግድ ዘርፍ ተሞክሯቸውን ያካፈሉት አቶ ሚካኤል ሀይሌ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያን ቡና ቆልቶ፣ ፈጭቶና አሽጎ ለብሪታንያ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ሰፊ እድል መኖሩን ባቀረቡት ጥናት አመላክተዋል፡፡
በለንደን ሊካሄድ የተዘጋጀው የቡና አውደ ርዕይ በዘርፉ እያጋጠመ ያለውን የካፒታልና የቴክኖሎጂ ችግር ለመቅረፍ፣ ከብሪታንያ ቡና ተረካቢዎች ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ፣ ቡናው ተቆልቶና ተፈጭቶ የሚገባበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ያለመ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መረጃ ያመላክታል።