Fana: At a Speed of Life!

ወቅታዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረጉ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ይበልጥ አጠናክሮ መሥራት እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረጉ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ይበልጥ አጠናክሮ መሥራት እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናገሩ፡፡
በአፍሪካ አገራት የሚገኙ ሚሲዮኖችን የ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና በቀጣይ የ60 ቀናት እቅድ ዙሪያ ከሚሲዮኑ መሪዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
የሚሲዮኖቹ አፈጻጸም በምን ደረጃ ላይ እንዳለ የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል የሆኑት አምባሳደር ፍስሃ ያብራሩ ሲሆን÷ መሻሻል የሚገባቸው ጎዳዮች ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እያንዳንዱ ሚሲዮን ባደረገው የስራ እንቅስቃሴ ያለባቸውን ጥንካሬና ክፍተት በመገምገም በቀጣይ ቀሪ ጊዜያት ትኩረት ሰጥተው መስራት በሚገባቸው ስራዎች ላይ መመሪያ ሰጥተዋል።
በበጀት ዓመቱ ቀሪ ጊዜያት በእቅድ ላይ ከተያዙ ስራዎች ባሻገር ወቅታዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረጉ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን በመሥራት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መንቀሳቀስ ይገባልም ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት የዓለም ጂኦ ፖለቲካዊ አሰላለፍ መልኩን እየቀያየረ መሆኑን በማንሳት ኢትዮጵያ እያንዳንዱን እርምጃዋን ከብሔራዊ ጥቅሟ አኳያ እየመዘነች ምክንያታዊ እና የተጠና አካሄድ መከተል አለባት ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.