Fana: At a Speed of Life!

ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ተመድ የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋገጠ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ የድርጅቱ የኢትዮጵያ ፅህፈት ቤት አስተባባሪ ገለፁ።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ጋር ተወያይተዋል።

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ÷ የኮሚሽኑን ዓላማና ምስረታ፣ አወቃቀር፣ የአገራዊ ምክክር አሰራር ሂደት፣ የእስካሁኑ ቅድመ-ዝግጅት ምዕራፍ ክንውኖችና ቀጣይ የዝግጅትና ትግበራ ሂደትን ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ አብራርተዋል።

በማብራሪያቸው ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ ያገኘ፣ የተለመደ የልሂቃን ውይይት ሳይሆን ከታችኛው ህብረተሰብ ጀምሮ ሁሉን አሳታፊና ሀሳብ የሚንሸራሸርበት፣ በግልፀኝነትና ተጠያቂነት መርሆች የሚመራ ነው ብለዋል።

አገራዊ ጉዳዮች በሚገባ ውይይት ተደርጎባቸው ብሔራዊ ዕርቅን ዕውን ለማድረግ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ዝግጀት ምዕራፍ እየገባ መሆኑንም ተናግረዋል።

አገራዊ ምክክሩ የሚመራው ካለምንም የውጭ ጣልቃገብነትና ጥምዘዛ በኢትዮጵያዊያን እንደሆነና ለዴሞክራሲም ትልቅ አሻራ ጥሎ የሚያልፍ እንደሆነም ተናግረዋል።

በዚህም የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብም ለዚህ ብሔራዊ ምክክር ፕሮጀክት ስኬታማነት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር የቭጊኒ ተርኪን፥ ኮሚሽኑ ብሔራዊ እርቅን እውን በማድረግና የኢትዮጵያን ሕልውና በማረጋገጥ ወደ ተሻለ ደረጃ ያሻግራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪ ዶክተር ካትሪን ሶዚ፥ ለተመድ ጠንካራ አባሉ የሆነችውን ኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት ይደግፋል ብለዋል።

ከኮሚሽነሮች ጋር ያደረጉት ውይይት ፍሬያማ መሆኑን እና ከኮሚሽኑ ምስረታ ጀምሮ ተመድ ድጋፍ እንዳደረገ ጠቅሰው፥ ለምክክሩ ስኬታማነትም ተመድ የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፕራክ አለፕ፥ ኢትዮጵያና ቱርክ በክፉ ጊዜም የሚተሳሰቡ ወዳጅ አገሮች መሆናቸውን በመግለፅ ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት ቱርክ ድጋፏን እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።

አገራዊ ችግሮችን ለመፍታት ምክክር ወሳኝ መሆኑን የገለጹት አምባሳደሯ፥ የኢትዮጵያን መልከ-ብዙ ችግሮች በውይይት ለመፍታት ኮሚሽነሮቹ ቀርጠኛ መሆናቸውን ተገንዝበናል ነው ያሉት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.