በድሬዳዋ ”ለፍቅር እሮጣለሁ” በሚል መሪ ሃሳብ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬዳዋ ከተማ ”ለፍቅር እሮጣለሁ” በሚል የ5 እና የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ተካሄደ።
በውድድሩ ላይ ከአንድ መቶ በላይ ታዋቂ ወንድና ሴት አትሌቶች እና በሺዎች የሚቆጠሩ የከተማዉ ነዋሪዎች ተሳትፈውበታል፡፡
መነሻና መድረሻውን ድሬዳዋ ምድር ባቡር አደባባይ ያደረገና የከተማዋን ዋና ዋና ጎዳናዎችን ያካተተውን ውድድር የድሬዳዋ ስፖርት ኮሚሽን ከሔማ ሬስ ኢንተርናሽናል ጋር በመተባበር አዘጋጅተዋል።
የዉድድሩ ዓላማ ድሬዳዋ የምትታወቅበት የፍቅርና የአብሮነት ዕሴቶች በይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ስለመሆኑ በአዘጋጆቹ ተገልጿል።
በተካሄደው የ10 ኪሎሜትር ወድድር በሴቶች እመቤት ንጉሴ 1ኛ ስትወጣ፣ ያለም ጌጥ ያረጋል እና አዳኔ አንማው ከውሃ ስራዎች ስፖርት ክለብ 2ኛ እና 3ኛ ወጥተዋል።
በወንዶች ገመቹ ጊሼ ከፌደራል ፖሊስ 1ኛ፣ ደበበ ተካ ከፌደራል ማረሚያ 2ኛ እንዲሁም ሙሉጌታ አሰፋ ከመከላከያ 3ኛ በመሆን ወድድራቸውን አጠናቀዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች በዚህ ውድድር ላይ 5ኪሎ ሜትር የሸፈነ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር አድርገዋል።
ለውድድሩ አሸናፊዎች ሜዳሊያና የገንዘብ ሽልማት ያበረከቱት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ፥ ስፖርት ጤናው የተጠበቀ አምራች ዜጋ ለመፍጠር ጉልህ ሚና የሚጫወት በመሆኑ በድሬዳዋ ከተማ ህብረተሰቡ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የማድረግ ባህሉ እንዲዳብር እሁድን ከትራንስፖርት እንቅስቃሴ ወጪ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
እንደዚህ ዓይነት ውድድሮች የአስተዳደሩን ስፖርት ከማጠናከር አኳያ ፋይዳቸው ከፍተኛ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በውድድሩ ከአንደኛ እስከ ሦስትኛ ለወጡ የሚዳሊያና ከ50 ሺህ እስከ 15 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት እንዲሁም ከ4ኛ እስከ 10 ኛ በመውጣት ውድድራቸውን ላጠናቀቁትም ከ10 ሺህ እስከ 6 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በውድድሩ ላይ የሔማ ሬስ ኢንተርናሽናል ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ጌጤ ዋሚ ፣ ሻለቃ አትሌት አሊ አብዶሽና አትሌት ሰንበሪ ተፈሪ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።
በተሾመ ኃይሉ