ፈረንሳይ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገሯ የገቡ የኢትዮጵያ ቅርሶችን ልትመልስ ነው
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 10 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ፈረንሳይ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገሯ የገቡ የኢትዮጵያ ቅርሶችን ልትመልስ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ከ15ኛው ክፍለ ዘመን እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ጅማሮ ባሉት ዓመታት ውስጥ የተሰሩት ቅርሶቹ ከሶስት ዓመታት በፊት በሕገ-ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ወደ ፈረንሳይ ከተጓጓዙ በኋላ በፓሪስ ሮይሲ አውሮፕላን ማረፊያ የተያዙ ናቸው ተብሏል፡፡
በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከጉምሩክ ባለስልጣን ጋር በጉዳዩ ላይ የተወያየ ሲሆን ቅርሶቹ በመጪው ሰኔ ወር እንደሚመለሱ ተመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 125ኛ ዓመት በሚያከብሩበት በዚህ ወቅት የቅርሶቹ መመለስ የሁለቱን ሀገራት በባህል ዘርፍ ያላቸውን ጠንካራ ትስስር የሚያመላክት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
ከዚህ ባለፈም የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑዌል ማክሮን በሕገ-ወጥ መንገድ የተጋዙ የአፍሪካ ቅርሶችን ለመመለስ ቃል መግባታቸውን ተከትሎ የፈረንሳይ መንግስትን በጉዳዩ ላይ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያልም ነው ያለው።