የኮሮና ቫይረስ ማዕከላዊ የነርቭ ክፍልን ሊያጠቃ እንደሚችል የቻይና የህክምና ባለሙያወች አስጠነቀቁ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 27 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሮና ቫይረስ ማዕከላዊ የነርቭ ክፍልን ሊያጠቃ እንደሚችል የቻይና የህክምና ባለሙያወች አስጠንቅቀዋል።
ቫይረሱ በስርዓተ ነርቭ ላይ የሚያደርሰው የጤና ችግር በልብ እና በመተንፈሻ አካላት ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት የከፋ መሆኑን በቤጂንግ የዲታን ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች አስታውቀዋል።
የህክምና ባለሙያዎቹ ማስጠንቀቂያ በኮሮና ቫይረስ ተጠቅቶ በሆስፒታሉ ሕክምናውን ሲከታተል የነበረ የ56 ዓመት ጎልማሳ የአዕምሮ ክፍል መጠቃቱን ተከትሎ የተሰጠ ነው ተብሏል።
ግለሰቡ በሆስፒታሉ ከአንድ ወር በላይ የህክምና ክትትል ሲደረግላቸው ከቆዩት የቫይረሱ ተጠቂዎች መካከል የአዕምሮው ክፍል የተጠቃ ብቸኛው ሰው ነው ተብሏል።
እንደ ህክምና ባለሙያዎቹ ገለጻ የቫይረሱ ተጠቂዎች ነገሮችን የመረዳትና የማገናዘብ አቅም መቀነስ የኮሮና ቫይረስ ስርዓተ ነርቭን ማጥቃት የሚችልበት ዕድል እንዳለው ማሳያ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ተጨማሪና ሰፋ ያሉ ምርምሮች እንደሚደረጉም ሆስፒታሉ ገልጿል።
የኮሮና ቫይረስ ተጠቂወች ለመተንፈሻ አካላት፣ ኩላሊት እና የልብ ህመም ይጋለጣሉ።
ዲታን ሆስፒታል በፈረንጆቹ 2003 ተከስቶ የነበረውን የሳርስ ወረርሽኝ ለመከላከል በተደረገው ጥረት ቁልፍ ሚና የተጫወተ የህክምና ተቋም መሆኑ ይነገራል።
ምንጭ፦ ሲ ጂ ቲ ኤን
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision