Fana: At a Speed of Life!

ለሀገር በቀል ምርቶች ዕውቅና ልንሰጥና አምራቾችን ልናበረታታ ይገባል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገራችን ምርት መኩራትን በመናገር ብቻ ሳይሆን ገዝተን በመጠቀም ለሀገር በቀል ምርቶች ዕውቅና ልንሰጥና አምራቾችን ልናበረታታ ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

12ኛው የአዲስ አበባ የቴክኒክ ሙያና ቴክኖለጂ ሳምንት አውደ ርዕይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት በወዳጅነት ፓርክ ለጎብኝዎች እይታ ክፍት ተደርጓል፡፡

የአዲስ አበባ ቴክኒክ ሙያ ስልጠናና ልማት ቢሮ ‘’ሙያና ቴክኖሎጂ ለምርታማነት’’ በሚል መሪ ሃሳብ የከተማ ነዋሪዎችን የቴክኖሎጂ ፍላጎትና የልማት እንቅስቃሴ የሚደግፉ በቴክኒክ ሙያ ተቋም የተፈበረኩ አገር በቀል የፈጠራ ውጤቶች ዓውደ ርዕይና ኤግዚቢሽን ነው ለተከታታይ ቀናት ለተጠቃሚዎች ክፍት የተደረገው፡፡

ኢንዱስትሪ፣ የፈጠራ ስራና ቴክኖሎጂን የከተማ አስተዳደራችን ለሕዝባችን የገባውን ቃል አንድ በአንድ ለመመለስ እንዲችልና ሕዝባችንን ተጠቃሚ ለማድረግ ዓይነተኛ ቁልፍ መሣሪያዎቻችን ናቸው ብለን አምነን ከሚመለከታቸው ሁሉ ጋር በጋራ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል ከንቲባዋ ።

በሀገራችን ምርት መኩራትን በመናገር ብቻ ሳይሆን ገዝተን በመጠቀም ለሀገር በቀል ምርቶች ዕውቅና ልንሰጥና አምራቾችን ልናበረታታ ይገባል ያሉት ከንቲባ አዳነች ፥ የአገርን ኢኮኖሚ ከቃላት ባለፈ በተግባር የምንደግፍበትም አይነተኛ መንገድ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር በከር ሻሌ በበኩላቸው ፥ ክህሎት በራስ የመተማመን ምንጭ ነው ብለው በራስ መተማመን ደግሞ ለፈጠራ ስራዎች ሁሉ መክፈቻ ቁልፍ በመሆኑ ከችግሮቻችን ሁሉ በቶሎ ለመውጣት አገር በቀል የፈጠራ ሥራዎችን በሙሉ አቅማችን ልንደግፍ ይገባል ብለዋል።

ተጠቃሚዎች ለተከታታይ ቀናት ወዳጅነት ፓርክ እየመጡ ምርቶችን እንደየፍላጎቶቻቸው ገዝተው በመጠቀም አምራቾቸንና አገር በቀል ፈጠራን ማበረታታት እንዲችሉ ኤግዚቢሽንና አውደ ርዕዩ ክፍት መሆኑም ነው ከከተማው ከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ የሚያመላክተው።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.