ኮሚሽኑ የ2022 ቨርዥን የታሪፍ መጻሕፍትን የዓለም የጉምሩክ ድርጅት ካስቀመጠው ጊዜ ቀድሞ መተግበሩ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉምሩክ ኮሚሽን የ2022 ቨርዥን የታሪፍ መጻሕፍትን የዓለም የጉምሩክ ድርጅት ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ ቀደም ብሎ መተግበሩ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት መሆኑ ተገለጸ፡፡
በዓለም የጉምሩክ ድርጅት ድጋፍ እና በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አስተባባሪነት በ2022 ቨርዥን የታሪፍ ማሻሻያ ላይ በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት የተካሄደው የአፍሪካ የጉምሩክ ባለሙያዎች ውይይት ተጠናቋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የእቃዎች የታሪፍ አመዳደብ ስርዓት ውስብስብ እና ተለዋዋጭ ባህሪ ያለው መሆኑን ጠቅሰው÷”የ2022 የታሪፍ ማሻሻያ እነዚህን ችግሮች የሚቀርፍ እና ድንበር ዘለል የንግድ እንቅስቃሴን ለማቀላጠፍ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያም የ2022 ቨርዥን የታሪፍ መጻሕፍትን የዓለም የጉምሩክ ድርጅት ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ መተግበሯን ኮሚሽነር ደበሌ ጠቁመው÷ “ይህም ለጉምሩክ ኮሚሽንም ሆነ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል”፡፡
ኮሚሽኑን ብቁ እና ተወዳዳሪ ለማድረግ ዘመናዊ ቴክኖሎጅዎችን ለመተግበር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
በውይይቱ የዓለም የጉምሩክ ድርጅት ተወካዮች፣ የአፍሪካ ሀገራት የጉምሩክ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡
ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት÷ የኢትዮጵያ ተሞክሮ ለሌሎች ሀገራት በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዓለም የጉምሩክ ድርጅት የታሪፍ መጻሕፍትን በየአምስት ዓመቱ በማሻሻል አባል ሀገራቱ ተግባራዊ እንዲያደርጉት የሚሰራጭ መሆኑን የኮሚሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!