Fana: At a Speed of Life!

በማምረቻና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ውዝፍ እዳ ላለባቸው ግብር ከፋዮች ቅጣታቸው እንዲነሳ መደረጉ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በማምረቻ እና ኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ውዝፍ እዳ ያለባቸው ግብር ከፋዮች ቅጣታቸው ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ በማድረግ ለችግሮቻቸው መፍትሄ መሰጠቱን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።

በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ከግብር አወሳሰን ጋር ተያይዞ ያለባቸውን ውዝፍ እዳ አከፋፈል በተመለከተ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ሲያቀርቡ መቆየታቸው የተገለፀ ሲሆን፥ ለዚህም ሚኒስቴሩ ችግሮቹን በትኩረት በመመልከት መፍትሄ መስተጡን ነው ያስታወቀው።

የገቢዎች ሚኒስቴር በማምረቻ እና በኮንስትራክሽን ዘርፍ ከተሰማሩ ግብር ከፋዮች ጋር በዛሬው እለት ውይይት ማካሄዱን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፥ የግሉ ዘርፉ ማደግ ለሃገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው በማንሳት፤ ይህ የሚሆነው ደግሞ መንግስት ተገቢውን ድጋፍ ሲያደርግ ነው ብለዋል።

ሚኒስቴሩ ውዝፍ እዳ ያለባቸው ግብር ከፋዮች ቀደም ሲል የባንክ ዋስትና ሳያቀርቡ እዳቸውን እንዳይከፍሉ የሚያስገድደውን አሰራር በማስቀረት ግብር ከፋዮች ውዝፍ እዳቸውን በተራዘመ የጊዜ ገደብ መክፈል እንዲችሉ መደረጉን ገልፀዋል።

ግብር ከፋዮች የነበረባቸውን ቅጣት ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝም አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል ሚኒስትሯ።

በዋናነት ይህ የመፍትሄ አቅጣጫ የተቀመጠበት ምክንያት መንግስት በማኑፋክቸሪንግና ኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ለማበረታታት እንዲሁም ድርጅቶቹ ተቀጥረው የሚሰሩ ሠራተኞች እንዳይበተኑና የቤተሰብ አስተዳደሪዎች ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ለሌላ ችግር እንዳይጋለጡ ተብሎ መንግስት ለዘርፉ ድጋፍ ለማድረግ ታስቦ መሆኑን አንስተዋል።

በውይይቱ የተሳተፉት ግብር ከፋዮችም የማምረቻና ኮንስትራክሽን ሴክተሩን ለማበረታታት እና ለመደገፍ በሚኒስቴሩ በኩል የተወሰደው እርምጃ የሚበረታታ መሆኑን ገልፀዋል።

ከሃሰተኛ ደረሰኝ እና ከሰነድ አያያዝ ጋር የሚነሱ ችግሮች በደንብ ሰፋ ተደርጎ ቢታይ ሲሉ አስተያየታቸውን አንስተዋል።

ከግብር አከፋፈል ጋር በተያያዘ የሰነድ አያያዝና የሃሰተኛ ደረሰኝ ዋነኛ ችግሮች መሆናቸውን ያነሱት ተሳታፊዎቹ ሃሰተኛ ደረሰኝ ነው ተብሎ ውሳኔ ሲሰጥ ተጠያቂው ገዢው ብቻ ሳይሆን ሻጩም ተጠያቂ ቢደረግ መፍትሄ ማግኘት እንደሚቻልም በተሳታፊዎቹ ተነስቷል።

ሚኒስቴሩ በተለይ ከሂሳብ አያያዝና አጠቃላይ ሰነድ ላይ ባለሃብቶች ሰራተኞቻቸውን ማብቃት እንዳለባቸውና ለዚህም ስልጠና በመስጠት ድጋፉን ሊያደርግ ፍቃደኛ መሆኑንም የሚኒስቴሩ የህግ ተገዥነት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘመዴ ተፈራ በውይይቱ ገልፀዋል።

ከግብር አከፋፋል ጋር ተያይዞ የሚነሱ ዘርፈ ብዙ ቅሬታዎችን ለማስቀረት ሚኒስቴሩ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር መድረኮችን በማዘጋጀት በቅንጅት ቢሰራ የሚነሱ ችግሮችን መቀነስ እንደሚቻልም ተሳታፊዎቹ አንስተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.