በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የሚከሰቱ ግጭቶችን ከመሠረቱ ለመፍታት የሚያስችል ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የሚገኙ የየዞኖቹ የሰላም ኮሚቴ አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች የሚከሰቱ ግጭቶችን ከመሠረቱ ለመፍታት የሚያስችል ውይይት አካሂደዋል።
በደብረብርሃን ከተማ በተካሄደው ውይይት፥ በባለፉት ጊዜያት በተደጋጋሚ እየተከሰተ ባለው ችግር የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞንና የሰሜን ሸዋ ዞን የይፋት ቀጠና ሕዝብ ቀጥተኛ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ሆነው ለሰው ሕይወት መጥፋት፣ ለአካል መጉደልና ለንብረት ውድመት መነሻ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ይህ ችግር ያበቃ ዘንድ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና የፖለቲካ መሪዎች የበኩላቸውን ሚና መወጣት አለባቸው ብለዋል የሀገር ሽማግሌዎቹ።
የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ተጣልቶ አያውቅም፤ አይጣላምም፤ ሁልጊዜ የፀብ ምንጭ የሆኑት አካላት በሁለቱም ወገን ያሉ ጥቂት ፅንፈኞች፣ ከግጭት አትራፊዎች እንዲሁም የደም ነጋዴዎች ናቸው ያሉት ተወያዮቹ፥ ይህንን ለማስተካከል ደግሞ ከልብ መነጋገር እንደሚገባ ገልጸው፥ የመንግስት አካላትም የሕግ የበላይነትን በቀጠናው ማረጋገጥ አለባቸው ሲሉ አፅዕኖት ሰጥተዋል።
እስካሁን የተካሔደው ግጭት መነሻው ምንድነው ብሎ በውል ለይቶና ለዚሁ ችግር ዘለቄታዊ መፍትሔ አበጅቶ መሔድ ከሁሉም አካል እንደሚጠበቅ መገለፁን ከብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ተወያዮቹ ሥር ነቀል መፍትሔ ይመጣ ዘንድ በራሳችን ተነሳሽነት እንደተሰባሰብነው ሁሉ ለመፍትሔውም፣ ሕዝብን ከሕዝብ አቀራርቦ መፍትሔ ለመሻትና ሰላምን በቀጠናው ለማምጣት እንሰራለን ሲሉ መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡
ተወያዮቹ ማንኛውም የመንግስት አካል እንደ ሰበብ የሚቆጥራቸውን ነገሮች ትቶ ለዘላቂው ሰላም ይሰራ ዘንድም ጠይቀዋል።
ሰላምን በማምጣት ሂደትም የሁለቱም ዞን የሕዝብ ሰላምና ደህንነት መምሪያ ኃላፊዎች እንደ መንግሥት አካል የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።