Fana: At a Speed of Life!

የቱሪዝምን ሃብቶቻችንን በማልማት የብልጽግና ጉዟችንን እውን እናደርጋለን – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቱሪዝም ሃብቶቻችንን በማልማት የብልጽግና ጉዟችንን እውን እናደርጋለን ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
 
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት “አዲስ እሳቤ ለቱሪዝም” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ የሚገኘውን 35ኛው የዓለም የቱሪዝም ቀን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል፡፡
 
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
 
የቱሪዝም ሃብቶቻችንን በማልማት የብልጽግና ጉዟችንን እውን እናደርጋለን!
 
35ኛው የዓለም የቱሪዝም ቀን “አዲስ እሳቤ ለቱሪዝም” በሚል መሪ ቃል መከበር ጀምሯል፡፡
 
ብዙዎች ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ እያሉ የሚጠሩት የቱሪዝም ዘርፍ ለአንድ ሀገር እና ህዝብ የሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ዋነኛ የእድገት ሚስጥር ነው፡፡
 
ሀገራችን ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፈ ብዙ የዳበረ ልምድ እና ዕውቀት ቢኖራትም ያሏትን የተፈጥሮ መስህቦች አልምቶ እና አስተዋውቆ ሰፊ የገቢ ምንጭ ከማግኘት አኳያ ገና ብዙ ርቀት ይቀራታል፡፡
 
በተለይም የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ተጠቅሞ ሀብት በማመንጨቱ ረገድ ብዙ ክፍተቶች አሉ፡፡ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን በመጠቀም ዜጎች ስለሀገራቸው የበለጠ እንዲውቁ እና ስለሀብቶቻቸውም በቂ መረጃ እንዲኖራቸው መስራት ወሳኝ ነው፡፡
 
የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ስናበረታታ በሀገር ውስጥ የሚገኙ እምቅ ሀብቶቻችንን በማስጎብኘት የፋይናንስ አቅም ከማሳደግ ባሻገር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር ህረብሔራዊ አንድነትን ከማጎልበት አልፎ የየአካባቢዎቹን እሴቶች እና ባህሎች አጉልቶ ለማሳየት ሰፊ ዕድሎችን ይፈጥራል፡፡
 
ሀገራችን በርካታ የማናውቃቸው ፀጋዎች ባለቤት ናት፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን ፀጋዎች በተገቢው መንገድ አልምቶ ወደ ሀብት እና እሴት በመቀየር የዜጎች ህይወት ለማሻሻል ዘርፉን ከሚመራው የመንግስት ተቋም በተለይም የቱሪዝብ ሚኒስቴር እና አጋር አካላት ብዙ ጥረቶች እና ስራዎች ይጠበቃሉ፡፡
 
ሀገራዊ ለውጡ ዕውን ከሆነበት 2010 ጀምሮ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አፍላቂነት እና መሪነት ለዘርፉ የተሰጠው ልዩ ትኩረት የሚያበረታታ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገበታ ለሀገር በሚል እሳቤ በሀገራችን የሚገኙትን የቱሪዝም መዳረሻዎች በዘመናዊ መልክ እንዲለሙ እና ለቀረው ዓለም እንዲተዋወቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ መዲናችን አዲስ አበባን ምርጥ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እጅግ በርካታ ስራዎች ተከውነዋል፡፡
 
በገበታ ለሸገር የተጀመረዉ ወዳጅነት ፓርክ፣ እንጦጦ እና አንድነት ፓርኮች የከተማዋን የቱሪዝም እሴት የጨመሩ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ በተጨማሪም የቱሪዝም መዳረሻዎች ከሆኑት እና በገበታ ለአገር ፕሮጀክት እየለሙ ካሉት መካከል ወንጪ፣ ጎርጎራ እና ኮይሻን በማልማት ቱሪዝሙን ወደላቀ የዕድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር እየተከናወኑ ያሉ አመርቂ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡
 
እነዚህ የተጀመሩ የቱሪስት መዳረሻዎች ተጠናክረው ወደ ስራ ሲገቡ በተለያዩ የሚዲያ አዉተሮች እንደተገለፀው በአፍሪካ ምርጥ የቱሪስት መዳረሻዎች ከመሆን አልፈው፤ የሀገራችንን ገጽታ ከስር መሰረቱ በመለወጥ ብቁ ተወዳዳሪ ለመሆን ያስችሉናል፡፡ በተጨማሪም ለብዙ ወጣት ተመራቂዎች የስራ ዕድሎችን በማመቻቸት የስራ አጥነትን ችግር እንደሚፈቱ ታምኖባቸዋል፡፡
 
ቱሪዝም ለሀገራችን የገቢ ምንጭ ብቻ ሳይሆን በዓለምአቀፍ ደረጃ ገፅታችንን አጉልቶ ለማሳየት ፋይዳው የላቀ ነው፡፡ ቱሪዝም በሀገራችን በርካታ ትሩፋቶችን እንዲያመጣ ከተፈለገ መሰረታዊ ማነቆዎቹን በመፍታት ስርነቀል የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ከሁሉም ባለደርሻ አካላት የሚጠበቅ ሀላፊነት ነው፡፡
 
እንዲሁም የግል ባለሀብቱ ወደዚህ ዘርፍ በመግባት ቢሳተፍ ራሱን እና ሀገሩን የመጥቀም ዕድል ይኖረዋል፡፡ በአጭሩ ይህን በስፋት ጥቅም ላይ ያልዋለ ትልቅ ፀጋ በአግባቡ በማልማት እና በማስተዋወቅ የቱሪስት ፍሰት መጠን እንዲጭምር በማድረግ ልማታችንን ማፋጠን ወሳኝ ነው፡፡
 
ቱሪዝም አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙትን የሰላም እና የፀጥታ ችግሮች በዘላቂነት በመፍታት ከዘርፉ የሚገኙ በረከቶችን መቋደስ የሚስፈልግበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡
 
መስከረም 15 ቀን 2015
አዲስ አበባ
 
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.