Fana: At a Speed of Life!

ከባድ የዘረፋ እና የውንብድና ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 14 የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ሥር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ እና አካባቢው ተደራጅተው ከባድ ዘረፋ እና ውንብድና በመፈፀም የሕዝብን ሰላም ሲያውኩ የነበሩ 14 የሽብር ቡድን አባላትን ባካሄደው ከፍተኛ ኦፕሬሽን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ገለጸ።
 
ግብረ ኃይሉ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፥ የከተማው ነዋሪ በስጋት እንዲኖር ከሽብር ቡድኑ ተልዕኮ ተቀብለው የሚንቀሳቀሱ ተላላኪዎችን የመመንጠሩ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
 
የውስጥ እና የውጭ ጠላቶቻችን ተደራጅተው ከከፈቱብን ዘርፈ-ብዙ ጦርነት አንዱ በከተማ የተሸሽጉ ተላላኪዎችን በመጠቀም በለስ ከቀናቸው በገሃድ፣ ካልሆነላቸውም በድብቅ የነዋሪውን ሰላም በማወክ ኅብረተሰቡ የደህንነት ዋስትና እንዳይሰማው በማድረግ በመንግሥት ላይ ያለውን ዕምነት ማሳጣት ዋነኛ ተልዕኳቸው ነው ብሏል ግብረ ኃይሉ።
 
ምንም እንኳን በተለያዩ ጊዜያት እኩይ ተግባራቸውን ለማሳካት ቢፍጨረጨሩም በኅብረተሰቡ መረጃ ሰጭነትና በፀጥታ ኃይሉ ብርቱ ጥረት በቁጥጥር ሥር እየዋሉ እንደሚገኙም ገልጿል።
 
የፀጥታ እና የደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ሰሞኑን ባካሔደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን በአዲሰ አበባ ከተማ በለሚኩራ ክፍለ ከተማ እና በሌሎች ክፍለ ከተሞች እየተንቀሳቀሱ ከባድ ዘረፋ እና ውንብድናን ጨምሮ የሞባይል ቴክኖሎጂን በመጠቀም በሕገ-ወጥ መንገድ ገንዘብ ሲያዘዋውሩ ከነበሩ 14 ተጠርጣሪዎች መካከል አምስቱ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
 
በዚህም መሠረት በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ፦ ኤርያስ ሐጎስ፣ ደሳለኝ ሓዱሽ፣ አያሌው ኃይሌ፣ ታደሰ ጣፈጠ እና ሐብቶም ወልዱ የተባሉት የዘረፋ ቡድኑ አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አብራርቷል።
 
በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች 10 የዘረፋ እና ከባድ ውንብድና ወንጀሎችን የፈፀሙ መሆናቸውንም አመላክቷል።
 
ግለሰቦቹ ስለፈፀሙት ወንጀል በተጨባጭ ማስረጃ የተረጋገጠባቸው ከመሆኑም ባሻገር ወንጀል መፈፀማቸውን አምነው ቦታውን እና አፈፃፀሙን ለምርመራ ቡድኑ መርተው አሳይተዋልም ብሏል።
 
ወንጀሉን ለመፈፀም ይጠቀሙበት የነበረ አንድ ሽጉጥ፤ 3 የብረት መቁረጫ፣ አንድ የብረት መፈልቀቂያ እና ሁለት ከፍተኛ ኃይል ያለው የፓውዛ መብራት እንዲሁም በርካታ ሐሰተኛ መታወቂያዎችን ጨምሮ የሚንቀሳቀሱበት ኮድ 1- 17267 የሆነ ሚኒ ባስ ታክሲ በፖሊስ ቁጥጥር መዋሉንም ነው ያስታወቀው።
 
በተጠርጣሪዎቹ ላይ 10 የምርመራ መዛግብት ተደራጅቶ ምርመራ የማስፋት ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ግብረ-ኃይሉ አስታውቋል።
 
በሌላ በኩል መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ከተማ ላይ በማድረግ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን በገንዘብ ለማጠናከር ተልዕኮ ተቀብለው ምሥጢራዊ የግንኙነት መስመር በመዘርጋት የሽብር ተልዕኮአቸውን የሚያስተላልፉበት “ቻናል 29” የሚባል የቴሌግራም አካውንት በመክፈት እና ስማቸው በቀላሉ እንዳይታወቅ በቀለም በማደብዘዝ ምሥጢራዊነቱን ጠብቀው ወንጀሉን መፈጸማቸውን ጠቁሟል።
 
የፀጥታ እና የደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ባደረገው ብርቱ ክትትል እና ጠንካራ ምርመራ ስማቸውን እና ለሽብር ዓላማ ማሳኪያ ይጠቀሙበት የነበረውን የባንክ ሂሳብ ቁጥራቸውን ማወቅ እንደቻለም ግብረ ኃይሉ አስታውቋል።
 
ቻናል 29ን በመጠቀም ሕገ-ወጥ ተግባሩን ሲፈፅሙ ከተገኙት መካከል፣ ቤላ ገብረዮሃንስ አብርሃ፣ ግርማይ ተክላይ አብርሃ፣ ፂዮን በርሔ ረዳ፣ ኢክራም አህመድ ሰይድ፣ ትርሐስ እቁባይ ይበይን፣ ሚካኤል ዘርዓይ ወልደ ጊዮርጊስ፣ እሌኒ ተስፋዬ ካሳ፣ ገብረ ህይወት በርሔ ገብረ ሚካኤል እና ገብረ አምላክ ገብረ መድህን አረጋዊ የተባሉት ተጠርጣሪዎች የሚጠቀሱ መሆናቸውን የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ገልጿል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.