Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ከ22 ሺህ በላይ ኩንታል ሲሚንቶ በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር ተያዘ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ተግባራዊ የተደረገው የሲሚንቶ ግብይት መመሪያ ከሚፈቅደው ውጪ በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የተገኘ 22 ሺህ 293 ኩንታል ሲሚንቶ ተይዞ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እየተስተዋለ ያለውን የሲሚንቶ ዋጋ ንረት ለመግታት የሲሚንቶ ግብይት መመሪያ ቁጥር 908/2014 አውጥቶ በመላው ኢትዮጵያ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል፡፡

የመመሪያው ዓላማ፥ በረጅም የግብይት ሰንሰለት አማካይነት ያለአግባብ እየናረ ያለውን የሲሚንቶ ዋጋ ለማስቀረት ብሎም በሀገራዊና ማህበረሰባዊ እድገት ላይ ፋይዳ ያላቸው የግንባታ ፕሮጀክቶች እንዳይስተጓጎሉና ቅድሚያ እንዲያገኙ ለማድረግ ነው፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ ፥ በተደረጉ የቁጥጥር ስራዎች 22 ሺህ 293 ኩንታል ሲሚንቶ በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር ተገኘቶ እርምጃ ተወስዷልል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ ውስጥም 15 ሺህ 179 ኩንታሉ ተወርሶ መሸጡንም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተጨማሪም 2 ሺህ 226 ኩንታሉ ተጣርቶ ህጋዊነቱን የሚያረጋግጡ መረጃዎች ተሟልተው ሲለቀቅ፥ ቀሪው መንግስት በተመነው ዋጋ መሸጡ ነው የተገለጸው፡፡

የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን፣ የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን፣ የሜጋ ግንባታ ፕሮጀክቶች ጽ/ቤት፣ የመንገዶች ባለስልጣን እና የዲዛይንና ግንባታ ሥራዎች ቢሮ ሲሚንቶ ቀጥታ ከፋብሪካዎች ገዝተው እንዲጠቀሙ በመመሪያው ተፈቅዶላቸዋል፡፡

ከነዚህ ውጪ ላለው የከተማዋ የሲሚንቶ ፍላጎት ከፋብሪካዎች በመረከብ በችርቻሮና በጅምላ የሚያቀርቡት የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት (ኢግልድ) እና የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ብቻ መሆናቸውም ነው የተጠቀሰው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.