10ኛው የጣና ፎረም ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 6 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለቀናት በባህር ዳር ሲካሄድ የቆየው 10ኛው የጣና ፎረም ተጠናቀቀ።
ጉባዔው የተካሄደው “የደኅንነት ሥጋቶችን መቆጣጠር ፣ተጽዕኖን የመቋቋም አቅምን በአፍሪቃ ለመገንባት” በሚል መሪ ቃል ነው፡፡
ፎረሙ በርካታ ነጥቦች የተነሱበትና ውጤታማ ውይይቶች የተስተናገዱበት ነውም ተብሏል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ÷ ከጉባዔው ጎን ለጎን ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ጋር በትብብር ለመስራት ስኬታማ ውይይቶች ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ሰላምና ደህንነትን በጋራ ከማረጋገጥ በተጨማሪ በአህጉሩ የተንሰራፋውን ድህነትና ኋላቀርነትን ለመቀነስ በተናጠል ከመስራት ይልቅ በጋራና በትብብር መስራት እንደሚገባን መግባባት ላይ ደርሰናል ነው ያሉት።
ጣና ፎረም አፍሪካውያን ህዝቦች ትስስር የሚፈጥሩበት፣ ባህልና ታሪካቸውን የሚጋሩበት፣ ለአህጉሩ የሚበጁ አዳዲስ ችግር ፈቺ ሐሳቦች የሚመነጩበት ተቋም ሆኖ እንዲቀጥል የክልሉ መንግሥት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ጉባዔው የተዘጋጀው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሠላም እና ደኅንነት ጥናት ተቋም ነው፡፡