Fana: At a Speed of Life!

በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት መንግስት የሚጠበቅበትን ተፈፃሚ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታኅ ሣሥ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት መንግስት በእሱ በኩል የሚጠበቁበትን ሙሉ ለሙሉ ተፈፃሚ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ወደ መቀሌ ያቀናው ከፍተኛ የመንግሥት ልዑክ አረጋገጠ፡፡

ዛሬ ወደ መቀሌ ያቀናው የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ከህወሓት አመራሮችና ከመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ተወያይቷል፡፡

ልዑኩ ከህወሓት አመራሮች እና ከመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ባደረገው ውይይት÷ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት መንግስት በእሱ በኩል የሚጠበቁበትን ሙሉ ለሙሉ ተፈፃሚ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች የመሰረተ ልማት አገልግሎቶች መጀመራቸው ይታወቃል፡፡

ይህን የመሰረተ ልማት አገልግሎት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ለማስጀመር ያስችል ዘንድ ዛሬ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ኃላፊዎች በመቀሌ ተገኝተው ከህወሓት አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ መብራት አገልግሎት፣ የመንገዶች ባለስልጣን፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የሌሎች ተቋማት ኃላፊዎች መሰረተ ልማቶቹን ማስጀመር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ያሉበትን ደረጃ ገልፀዋል።

በቀጣይ ያልተጀመሩ የመሰረተ ልማት አገልግሎቶችን በአጭር ጊዜ ለማስጀመር እንደሚሠራ አብራርተዋል፡፡

በተለይም ኢትዮ ቴሌኮም፣ ባንክ፣ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና አየር መንገድ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመቀሌና አካባቢው ሥራ ለማስጀመር እንቅስቃሴ ላይ እንደሆኑ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተወሰኑ ሙያተኞችን ሁኔታውን እንዲያመቻቹ መቀሌ እንዲቆዩ አድርጓል።

ልዑኩ ከህወሓት አመራሮች ባለፈ ከተወከሉ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ጋር የተወያየ ሲሆን፥ ነዋሪዎች የመጣው ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና ያልተጀመሩ መሰረተ ልማቶች በፍጥነት እንዲጀመሩ ጠይቀዋል።

ከፌዴራል መንግስት ልዑክ ወደ መቀሌ መምጣቱም መንግስት ለሰላም ስምምነቱ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በርካታ ለውጦች መኖራቸውን ጠቅሰው፥ ይህን ለውጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ለማሳየት ልዑኩ መቀሌ መገኘቱን አስረድተዋል።

ሰላም ለሁሉም ያስፈልጋል የሰላም አስፈላጊነትን ባለፉት ሁለት አመት አይተናል የእናቶች ሞት፣ ለቅሶ ይበቃል፣ የመሰረተ ልማት ውድመቶች ይበቃል ህዝባችን እረፍት እንዲያገኝ ማድረግ ይኖርብናልም ነው ያሉት።

ከዚህ በኋላ በስምምነቱ መሰረት የተደረሱባቸውን ጉዳዮች እየተነጋገሩ መፍታት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

የህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል በበኩላቸው፥ “ያለሶስተኛ ወገን እንደዚህ እኛው ችግሮቻችንን ለመፍታት መገናኘታችን ትልቅ እርምጃ ነው” ብለዋል።

አሁን ላይ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የተጀመረው የሰላም ሂደት በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው ሲሉም ይበልጥ የተቸገረውን ህዝብ ለመድረስ ስራዎች በፍጥነት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በታሪኩ ለገሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.