Fana: At a Speed of Life!

የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ለማዳረስ የጤና መድኅን መርሐ ግብርን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ መረባረብ ይገባል – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 22 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ለማዳረስ የጤና መድህን መርሐግብርን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ብሔራዊ ምክር ቤት ይፋዊ የስራ ማስጀመሪያ እና የጤና መድህን ትግበራ 10ኛ ዓመት ክብረ በዓል መርሐ-ግብር እየተካሔደ ነው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መንግስት የዜጎች የኑሮና የጤና ሁኔታን ለማሻሻልና ከድህነት ለማውጣት በርካታ ስትራቴጂዎችን ቀርጾ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና አገልግሎት መርሐ ግብር አብዛኛውን አርሶ አደር የሕብረተሰብ ክፍል የሚያቅፍ ወሳኝ የሆነ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

የጤና መድህን ስርዓት በሌሎች ሀገራት ያለውን ትግበራ በማንሳት በኢትዮጵያም በፍትሀዊነትና ተደራሽነት የበለጸገና ሀገሩን የሚወድ፣ ተስፋ የሰነቀ ማህበረሰብን ለመገንባት የጤና መድህን አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።

በቀጣይ ሁሉን አቀፍ የጤና መድህንን ተደራሽ ለማድረግ የበለጠ መረባረብ እንደሚገባ አቶ ደመቀ አስገንዝበዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የጤና መድህን ሽፍን ቁልፍ ድርሻ እንዳለው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አገልግሎቱ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በ894 ወረዳዎች ተግባራዊ በማድረግ 45 ሚሊየን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.