Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ-ቴሌኮምና ጌትፋክት ኢትዮጵያ “ብሩህ ትወልድ” የተባለ የትምህርት ፕሮግራም በጋራ ለማካሄድ ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ-ቴሌኮምና ጌትፋክት ኢትዮጵያ “ብሩህ ትወልድ” የተባለ የትምህርት ፕሮግራም በጋራ ለማካሄድ የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

የኢትዮ ቴሌ ኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በዚህ ወቅት ÷ ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚሰራው ስራ ውስጥ መሰል የዲጂታል ትምህርት ፕሮግራምን የያዙ ፕሮጀክቶች ደግሞ አጋዥ ናቸው ብለዋል።

የቴክኖሎጂን አቅም አሟጠን በመጠቀም መሰል የዲጂታል ፕሮጀክቶችን ፍሬያማ ለማድረግ እየሰራን ነው ያሉት ስራ አስፈጻሚዋ ፥ የትምህርትን ተደራሽነት ለማሳደግ የምንሰራውም ስራ አንዱ መሆኑንም ነው ያነሱት።

በቀጣይም በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውንና መሰል ሀገር ገንቢ ፕሮጀክቶችን ይዘው ሲመጡ በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የጌትፋክት ኢትዮጵያ መስራች ዶ/ር ብርሃኑ ቡልቻ በበኩላቸው ÷ የዳያስፖራው ማህበረሰብ ሀገሩን ለመርዳት ይህ ፕላትፎርም የመጀመሪያው መሰረት መሆኑንም ነው የጠቀሡት።

ሥምምነቱ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምሁራን በማሳተፍና የእውቀት ሽግግርን በማምጣት ማዕከላቱ የተቋቋሙበትን ዓላማ ማሳካት እንዲችሉ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ይሆናልም ብለዋል።

ጌትፋክት ኢትዮጵያ በሚያካሄደው የትምህርት ማትጊያና የሀገር ተረካቢ ወጣቶችን በእውቀት የማስታጠቅ ፕሮግራም በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር በተለያዩ ጊዜያት የሚጠናቀቁ አጫጭርና ለውጥ በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ ስልጠናዎችን መስጠት የሚያስችል ነው ተብሏል።

ጌትፋክት ኢትዮጵያ ነዋሪነታቸው በውጪ ሀገራት በሆኑ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተቋቋመ ድርጅት ነው።

በይስማው አደራው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.