Fana: At a Speed of Life!

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በተለያዩ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ባለሙያዎች አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በተለያዩ ሙያዎች ያሰለጠናቸውን ባለሙያዎች በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

ተቋሙ በፎቶ ካሜራ፣ በቪዲዬ ካሜራ ፣በቪዲዮ ኤዲቲንግና ግራፊክስ ክህሎት ቴክኒክ ያሰለጠናቸውን የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ሰራተኞችን ነው ያስመረቀው።

ሠልጣኞቹ ስልጠናውን ለአንድ ወር በሁለት ዙር ሲከታተሉ መቆየታቸው ተመላክቷል፡፡

በምረቃ መርሐ ግብሩ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የፌዴራል ፖሊስ አመራሮች ተገኝተዋል።

አቶ አድማሱ ÷ ሀገር የምትቆመው በጸጥታ አካላት ነው ፤ፌዴራል ፖሊስ የሀገር ምሰሶ ነው ፤ በዚህም ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመስራታችን እና ተቋሙን ለማገልገል እድሉን በማግኘታችን ደስተኛ ነን ብለዋል፡፡

ፌዴራል ፖሊስን ማገልገል ክብር ነው ያሉት ስራ አስፈፃሚው÷ በቀጣይም በትብብር እና በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የህዝብ የመረጃ ተቋም መሆኑን ገልፀው÷ መረጃዎችን በመሰብሰብ ሒደት ውስጥ የፀጥታ አካላት አጋዥ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

የአሁኑ ስልጠና ጅማሬ መሆኑንና ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው አቶ አድማሱ ያስገነዘቡት፡፡

የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የፎረንሲክ ምርመራ ምክትል ዋና መምሪያ ሃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ከተማ ደባልቄ በበኩላቸው÷ስልጠና ለፍትሕ ስራ አጋዥ መሆኑንና ለዚህም ፋና ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዛሬው ዕለት የተመረቁ ሰልጣኞች ከስልጠናው ባሻገር እራሳቸውን በተለያዩ መንገዶች እንዲያበቁም አሳስበዋል፡፡

በቀጣይ በምንፈልጋቸው ስልጠናዎች በተገባልን ቃል መሰረት ወደ ፋና እንመጣለን ያሉት ረዳት ኮሚሽነሩ÷ ለተደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በፌዴራል ፖሊስ የሰውሃብት አስተዳደር እና ድጋፍ አገልግሎት ምክትል ዋና መምሪያ ሃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አይሻ ደመና÷ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ለረጅም ጊዜ እንደሚያውቁ እና ተሳታፊ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ አብረው በመስራታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው ÷ ለሰልጣኞች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመጨረሻም ሰልጣኞቹ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ስቱዲዮን ጎብኝተዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.