ኢትዮጵያ 38 የሶማሊያ ፖሊስ መኮንኖችን በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት መርሐ ግብር ልታሰለጥን ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ 38 የሶማሊያ ፖሊስ መኮንኖችን በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት መርሐ ግብር ሊያሰለጥን መሆኑ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የመጀመሪያ ዲግሪና የሁለተኛ ዲግሪ ፖሊሳዊ ሳይንስን ለመቅሰም ከሶማሊያ ለመጡ የፖሊስ መኮንኖች የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል አድርጓል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ፥የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ለረጅም ዘመናት የጎረቤት ሀገራት የፖሊስ አመራሮችና አባላትን በማስተማር ለቀጠናው ሰላምና ደህንነት ግንባታ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽነር ጄነራሉ አያይዘውም ፥ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ተባብሮ መስራትና የፖሊስ ተቋማቱን በትምህርትና ስልጠና ማጠናከር ድንበር ተሻጋሪ ወንጀልን ለመከላከል እንደሚያግዝም ነው የተናገሩት።
በቅርቡም ኮሚሽኑ ከሶማሊያ ጋር በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የሶማሊያ ወጣት ፖሊስ አመራሮች ትምህርትና ስልጠና እንዲያገኙ የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል።
በዚህም የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ በተለያዩ የትምህርት ምርሃግብሮች 38 የሶማሊያ ፖሊስ መኮንኖችን በ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ለማስተማር መቀበሉን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።