Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ የኢትዮጵያን ሀገራዊ አንድነት ለመደገፍ ከኢትዮጵያ ጐን እንደምትቆም አረጋገጠች

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ እንደትናንቱ ሁሉ ዛሬም የኢትዮጵያን ሀገራዊ አንድነት ለመደገፍ ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትቆም አረጋገጠች፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ከሩሲያ ፖርላማ የአፍሪካ አገራት እና የሩሲያ ምክር ቤት የትብብር ሀላፊ ኒኮላይ ኖቪችኮቭ ጋር በፅህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ኒኮላይ ኖቪችኮቭን÷ ሩሲያ እንደትናንቱ ሁሉ ዛሬም የኢትዮጵያን ሀገራዊ አንድነት ለመደገፍ ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትቆም እና ይህም አቋሟ የማይለዋወጥ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ እንቅስቃሴዎች ሩሲያ በቅርበት የምትከታተል መሆኑን ገልፀው ኢትዮጵያ ለብዙ ሀገራት ምሳሌ በሚሆን መልኩ የሰሜን ኢትዮጵያን ችግር በአፍሪካ ጥላ ስር መፍታቷ የሚደነቅ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል አጋጥሞ የነበረውን ችግር ለመፍታት ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የሚለውን መርህ እንደ ሁነኛ ዘዴ አድርጋ ተጠቅማበታለች ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በሁሉም አካባቢዎች ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንና ይህም ለሩሲያም ሆነ ለሌሎች ሀገራት ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር በመሆኑ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ የሩሲያ ባለሀብቶች በስፋት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አፈጉባኤው በአፍሪካና ሩሲያ ምክር ቤቶች ጉባኤ ላይ እንዲሳተፉ ግብዣ እንደቀረበላቸው ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.