Fana: At a Speed of Life!

ለኢትዮጵያ ስጋት የሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ያስፈልጋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለኢትዮጵያ ወቅታዊ ስጋት የሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት መምህር ዶክተር ሚርጊሳ ካባ እንደገለጹት÷ የማህበረሰብ ጤና ከእንስሳት፣ ከከባቢ አየር፣ ከውሃ እና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡

ለአብነትም ኢቦላ እና ኮሮና ቫይረስን ጨምሮ 70 በመቶ የሚሆኑት በሽታዎች ከእንስሳት ወደ ሰው እና ከሰው ወደ እንስሳት የሚተላለፉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ የሚስተዋለው የከባቢ አየር መለዋወጥ ሁኔታም ችግሩን ይበልጥ እያሰፋው እና እያጠነከረው መምጣቱን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

ዘርፈ ብዙ የሆነውን የማህበረሰብ ጤና ችግር በአንድ ሴክተር ብቻ መከላከል እንደማይቻል ጠቅሰው፥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በተለይም የጤና፣ ግብርና፣ ገንዘብ እና ትምህርት ሚኒስትሮች እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ እና የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣኖች በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የብሄራዊ አንድ ጤና አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ፈይሳ ረጋሳ ÷ አንድ ጤና መርሐ ግብር ሀገራዊ የጤና ስጋቶችን ከመቀነስ አንጻር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2016 ጀምሮ የአንድ ጤና መርሐ ግብርን ቀርጻ እየተገበረች መሆኑን ጠቁመው÷በተለይም አባ ሰንጋ እና የእብድ ውሻ በሽታን መከላከል ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ አመርቂ ውጤት መገኘቱን ነው ያብራሩት፡፡

በቀጣይም ብሄራዊ ኮሚቴው ለኢትዮጵያ ስጋት የሆኑ በሽታዎችን በተናጠል ሳይሆን በጋራ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር እንዲሰሩ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት የአንድ ጤና ማሻሻያ ፕሮጀክት ጋር በቅንጅት እና በትብብር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በአውሮፓ ህብረት ድጋፍ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ11 የአፍሪካ ሀገራት እየተገበረ ሲሆን÷ በኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በቀጣይ በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያ የባለድርሻ አካላትን ሚና ማጎልበት አላማው ያደረገ የሁለት ቀናት አውደ ጥናት በአዲስ አበባ እያካሄደ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.