Fana: At a Speed of Life!

ተቋማቱ በጋራ መስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሀገራዊና ሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ታዜር ገ/እግዚአብሔር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ተፈራርመዋል።

ጀነራል ታዜር እንዳሉት÷ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከዕለታዊ ስራዎች ጀምሮ በስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ ከሚኒስቴሩ ጋር በቅንጅት ይሠራል።

የመግባቢያ ስምምነቱ የትብብር ሥራዎቹ ስርዓት የያዙና በሰነድ የተደገፉ እንዲሆኑ እንደሚያግዝም አመላክተዋል፡፡

ስምምነቱ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት የምታደርገውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያስችላትም አብራርተዋል።

ሁለቱ ተቋማት ለፖሊሲ ግብዕት የሚሆኑ ሐሳቦችን በጋራ ለማመንጨት የተመቻቸ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው መገለጹን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

አምባሳደር ብርቱካን አያኖ÷ ተቋማቱ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በመፈፀም በኩል በሥራ የሚገናኙባቸው ጉዳዮች በርካታ መሆናቸውን አንስተዋል።

በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ቢሮም ጭምር በመጋራት በትብብር የሚወጧቸው ተልዕኮዎች መኖራቸውንና በተለያዩ የሥራ እንቅስቃሴዎችም የመረጃ ልውውጥ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

የእስካሁኖቹ የጋራ ሥራዎች ስኬቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በተቋማቱ አመራሮች ቁርጠኝነት ላይ ብቻ ተመስርቶ የነበረውን የትብብር ግንኙነት በሰነድ የተደገፈ ለማድረግ የመግባቢያ ስምምነቱ መፈረሙን ገልጸዋል።

ስምምነቱ ዲፕሎማቶች የሀገር ጥቅምና ብሔራዊ ደኀንነት በማስጠበቅ ረገድ በቂ ዝግጅት እንዲኖራቸው ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሚያገኟቸውን የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እንደሚያጠናክር አብራርተዋል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.