Fana: At a Speed of Life!

የመታወቂያ እድሳትና የጋብቻ ምስክር ወረቀት ማረጋገጫ አገልግሎት በተጨማሪነት እሁድ ግማሽ ቀን እንዲሰጥ ይደረጋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የመታወቂያ እድሳትና የጋብቻ ምስክር ወረቀት ማረጋገጫ በመስጠት ሂደት ላይ ክፍተት የሚታይባቸው ወረዳዎች እሁድን እስከ 8 ሰዓት አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል ተብሏል።

በ14 ወረዳዎች ያጋጠመው የወሳኝ ኩነት አገልግሎት ችግርን ለመቅረፍ ቴክኖሎጂን የማዘመን ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በቦሌ ቡልቡላ ወረዳ 12 እና በኮልፌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 መታወቂያ ለማሳደስና የጋብቻ ምስክር ወረቀት ለመውሰድ ተገልጋዮች ሲጉላሉ ለማየት ችሏል።

በተለይም በቦሌ ቡልቡላ ወረዳ 12 ተገልጋዮች የወሳኝ ኩነት አገልግሎትን ለማግኘት ወረፋ ለመያዝ ጋቢና ብርድልብስ ለብሰው እስከማደር መድረሳቸውን ተገንዝቧል።

የቦሌ ቡልቡላ ወረዳ 12 የወሳኝ ኩነት ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታምራት ጅፋር ለተገልጋዮች እንግልት ምክንያቱ የተገልጋዩ ብዛትና የአገልግሎት አሰጣጡ አለመመጣጠን መሆኑን ተናግረዋል።

ነገር ግን ከስራ ሰዓት ውጪ ሌሊት 12 ሰዓት ጭምር ወደ ስራ በመግባት ችግሩን ለመቅረፍ እየሰሩ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

በኮልፌ፣ በየካ፣ በአቃቂ ፣ በልደታ እና በሌሎችም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በተመሳሳይ መታወቂያ ለማሳደስ እንዲሁም የጋብቻ ምስክር ወረቀት ማረጋገጫ ለማግኘት ተገልጋዮች እንደሚጉላሉ ለጣቢያችን አስተያየት ሰጥተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመልካም አስተዳደርና የአቤቱታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ብርሀኑ ረታ÷ በመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞች የቤት ችግርን ለመቅረፍ የከተማ አስተዳደሩ የነዋሪነት መታወቂያ በማቅረብ እንዲመዘገቡ መወሰኑን ተከትሎ በመታወቂያ አሰጣጡ ላይ ጫና መፈጠሩን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በልዩ ሁኔታ አዲስ መታወቂያ እንዲሰጣቸው የተፈቀደላቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የመከላከያ፣ የፌደራል ፖሊስ እና መምህራን መታወቂያ የመስጠት ሂደቱ ላይ ሌላው ጫና የፈጠረ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

በዋናነት ግን የሰው ኃይል እጥረት፣ የኢንተርኔት መቆራረጥ እንዲሁም የወረዳ ኔት የቴክኖሎጂ ስርዓት ፈጣን አለመሆኑ ለተገልጋዮች መጉላላት ምክንያት መሆኑን አንስተዋል።

ለዚህም ከተማ አስተዳደሩ ችግሩን ለመቅረፍ የአጭር እና ረጅም ጊዜ የመፍትሄ አማራጮችን በማስቀመጥ እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተረዋል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.