የምርጥ ዘር እጥረት እንዳያጋጥም እየተሠራ ነው- ግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ2015/16 የምርት ዘመን 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅረብ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ለክልሎች የሚደለድለው ምርጥ ዘር በኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የምርጥ ዘር ድርጅት እና ኮርቴቫ የተሰኘ በግል ምርጥ ዘር የሚያባዛ ድርጅት አማካኝነት የሚመረተው መሆኑ ተገልጿል፡፡
ቀሪው ደግሞ በየክልሎቹ በሚገኙ ምርጥ ዘር አባዥ ድርጅቶች በኩል እንደሚሸፈን ነው የተገለጸው፡፡
በሚኒስቴሩ የኢንቨስትመንትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) በርካታ የምርጥ ዘር ዓይነቶች መኖራቸውን ጠቅሰው÷ በቆሎ፣ ጤፍ እና ስንዴ በዋናነት አርሶ አደሩ የሚፈልጋቸው መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በዚሁ መሰረት በቆሎ ለሚዘሩ አካባቢዎች የበቆሎ ምርጥ ዘር እየተሰራጨ ነው ብለዋል፡፡
እንዲሁም የምርጥ ዘር አቅርቦት “በዚህ ጊዜ ይጠናቀቃል” ተብሎ ስለማይወሰን በየጊዜው እንደየአካባቢዎቹ የዘር ወቅት ሌሎቹ ምርጥ ዘሮች እንደሚቀርቡ አመላክተዋል፡፡
“እንደሀገር አርሶ አደሩ በቂ ምርጥ ዘር እያገኘ ነው የሚል ግምገማ የለምንም” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ÷ ለዚህም የጸጥታ ችግር በነበረባቸው አካባቢዎች ምርጥ ዘር በአግባቡ መሰብሰብ አለመቻሉን በምክንያትነት አንስተዋል፡፡
ይህን ለማካካስም በአንጻሩ የጸጥታ ችግር በሌለባቸው አካባቢዎች በስፋት ለማምረት እና ለማቅረብ ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
በተለይም አልፎ አልፎ የበቆሎ ምርጥ ዘር እጥረት እንደሚያጋጥም ገልጸው÷ እጥረቱን ለማቃለልም ሰፋፊ መሬት ወስደው በሚያመርቱ የግል ባለሃብቶች በኩል እንዲባዛ እየተደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!