Fana: At a Speed of Life!

ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሠጠ መግለጫ

የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድምና እህት ህዝቦች ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ሕልውና ለማስጠበቅ ያልከፈለው ዋጋ የለም፡፡ የኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማጽናትም ሲል ከመክፈል የሚሰስተው ዋጋ የለም፡፡ በመሆኑም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም ሆነ መላው የክልሉ ሕዝብ በሀገር ሕልውና እና በኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ ላይ ያለው አቋም የግዜ እና የሁኔታዎች መፈራረቅን ተከትሎ የማይለዋወጥ ጽኑ ሐቅ ስለመሆኑ በታሪክና በዜጎች ሕሊና እንዳይፋቅ ሆኖ የተከተበ እውነታ ነው፡፡

ስለሆነም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በክልላችን ውስጥ የሚተለሙም ሆነ የሚፈጸሙ ማንኛውም አይነት ተግባራት ከዚህ ብሔራዊ መዳረሻ አንጻር የሚቃኙ መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። ማንኛውም አይነት ተቋማዊ መዋሮች የሚደራጁበትም አልፋ እና ኦሜጋዊ አመክንዮ ይኸው ነው፡፡

ከሰሞኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ ዋና አጀንዳ ከሆኑት ብሄራዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነውና በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የልዩ ኃይል አደረጃጀቶችን መልሶ የማደራጀት ተግባር ዋነኛ እና ብቸኛ ምክንያትም ዓላማው የኢትዮጵያን ሕልውናን የበለጠ የማበርታት የጋራ ግብን ያነገበ፣ በተማላ አገራዊ ጥናት ላይ የተመሰረተ፣ የህዝቦችን አንድነትንና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የተተለመ እንዲሁም የጋራ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን እውን ለማድረግ በሁሉም ክልሎች ታምኖበት የተገባበት ወሳኝ ተግባር ነው።

የአማራ ክልል ልዩ ኃይል በክልሉ ከተመሰረተበት ግዜ ጀምሮ ከአገር መከላከያ ሰራዊትና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሆን የአማራ ክልልን ሕዝብ ሠላም እና ጸጥታን ለማስከበር በቅንነትና በቆራጥነት አገልግሏል፡፡ ከክልል አቀፍ ውለታው ባሻገር በኢትዮጵያ ሕልውና ላይ ተጋርጦ የነበረን ከፍተኛ አደጋ ለመቀልበስ ሲል ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድምና እህት ህዝቦች ጋር በመሆን በኢትዮጵያዊነት የላቀ ሥነ-ልቦናዊ ከፍታ ሁሉንም አይነት መስዋእትነት ከፍሎ ኢትዮጵያና አትዮጵያዊነት ላይ የተቃጣን አደጋ በታማኝነት አምክኗል፡፡ ይህ አኩሪ ገድልና ውለታ ሁልጊዜም በታሪክና በትውልድ ልቦና ውስጥ እየተዘከረና ጽንቶ የሚኖር ታላቅ ተግባር ነው፡፡

ይህን መሰሉን ብሔራዊ ውለታ የበለጠ ለማጎልበትና ለማስፋት የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት አማራ ክልል ጨምሮ በሁሉም ክልላዊ መንግስታት ውስጥ የሚገኙ የልዩ ኃይል አደረጃጀቶችን ያሰባሰበ በጥናት ላይ የተመሰረተ መልሶ የማደራጀት ስራ በሁሉም ክልሎች በየደረጃው ካለው የፀጥታ አመራር፣ የመንግስት አመራር፣ የልዩ ኃይል አመራርና አባላት፣ በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት የተደረገበትና እየተደረገበት ያለ በሂደት ላይ የሚገኝ የጋራ አገራዊ ተግባር ነው።

ይህ የልዩ ኃይል ፓሊስ አደረጃጀቶችን መልሶ የማደረጃት ወይም የሪፎርም ስራ በሁሉም የፌደራልና ክልላዊ መንግስታት መሪዎች የጋራ ስምምነትና እንደ አንድ ሀገር አንድ ጠንካራ የፌድራልና የክልል የፀጥታ መዋቅር እንዲኖረን ታስቦ የተለያዩ ማራጮች ለልዩ ኃይል አባላቶቻችን ያቀረበ እና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በኩር ያደረገ ሀገር አቀፍ ታሪካዊ ተግባር ነው፡፡ ተግባሩም ለሁሉም ክልል የልዩ ኃይል አደረጃጀቶች የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌድራልና የክልል መደበኛ ፓሊስ ፣ የፌድራልና የክልል የማረሚያ ቤቶችን ፓሊስ አባል እንዲሆኑ አማራጮች ያቀረበ ብሔራዊ ተግባር ነው።

በቅርቡ በመንግስት የተጀመረው የልዩ ኃይል ፓሊሶች የሪፎርም ተግባር እውነታዉ ከላይ በተቀመጡት አማራጮች ለሁሉም ክልሎች የልዩ ኃይል አባላት እንደ የፍላጎታቸው በቀረቡት አማራጮች እንዲካተቱ ታሳቢ ያደረገ የፌድራልና የክልል የፀጥታ አካላትን የማጠናከር በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ የሚገኝን ብሔራዊ ተግባር ነው።

ይሁን እንጅ እውነታዉ ይሄ ሆኖ ሳለ አንዳንድ አካላት የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን አየር ላይ እንዲበተን እየተደረገ ነው የሚል ከእውነት የራቀ ፍፁም በተሳሳተ መንገድ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት የአማራን ሕዝብ ውስጣዊ ሠላምና አንድነት የሚያደፈርስ፣ የልዩ ኃይሉን አንድነት የሚረብሽ፣ ባልተገባ መንገድ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርጉ እንቅስቃሴ ላይ ተጠምደው ይገኛሉ።

 

ድርጊቱም ህዝባችንና የልዩ ኃይል አባሎቻችንን በተጨባጭ እየረበሸ ይገኛል። ስለሆነም መላው የልዩ ኃይል አባላትና መላው የክልሉ ህዝብ እንዲገነዘቡት የምንፈልገው መንግስት ይህንን የመልሶ ማደራጀት ስራ የሚከውነው የልዩ ኃይላችንን የሰው ኃይል ለበለጠ ፋይዳ ላለው ተልዕኮ መልሶ የማደራጀትና ብቁ የማድረግ አገራዊና ክልላዊ ፋይዳ የማዘጋጀት ተግባር እንጅ በመልሶ ማደራጀቱ ሂደት ምንም አይነት የሚበተንም ኃይል የሌለ መሆኑን ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል።

ስለሆነም መላው የአማራ ሕዝብ በአንዳንድ አፍራሽ የሚዲያ ቡድኖች በሚነዛው አሉቧልታ ሳይታለልና ሳይደናገር እንደ አንድ ሕዝብ ያለውን ታሪኩን እና ስነ ልቦናውን በሚመጥነው የኢትዮጵያዊነት ላእላዊ ማእቀፍ ጥላ ስር በመሰባሰብ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊ አንድነትን የማጽናት ሂደትን እንዲደግፍ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

የተከበራችሁ የክልላችን ህዝቦች የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን ሕዝብ መብትና ጥቅም የሚጋፋ የትኛውንም አይነት ውሳኔ ተግባራዊ እንደማያደርግ ሕዝባችን ሊያውቀው ይገባል።

የተከበራችሁ የክልላችን የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት እንዲሁም መላው ሕዝባችን ለራሳቸው ጥቅምና ፖለቲካዊ ዓላማ ሲሉ ክልላችንን የትርምስ ቀጠና ለማድረግ ከሚሠሩ አካላት ራሳችሁን በመጠበቅ የክልላችን የፀጥታ ኃይል ብቁ ዘቦች ሁናችሁ ሰላምና ፀጥታን በማስጠበቅ ሥራችሁ እንድትተጉ እያሳሰብን የተጀመረውን ልዩ ኃይሉን መልሶ የማደራጀት ስራ መላው ህዝባችንንና ልዩ ኃይላችንን በማወያየት እና በመተማመን የሚፈፀም በመሆኑ በየካምፓችሁ ወይም በየተመደባችሁበት የስራ ቦታ ተረጋግታችሁ በትግስት እንድትጠብቁ የክልሉ መንግስት ጥሪውን ያስተላልፋል።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት

መጋቢት 29/2015 ዓም

ባሕር ዳር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.