Fana: At a Speed of Life!

የሱዳን ሕዝብ አሁን ካጋጠመው ሁኔታ ለመውጣት የሚያስችለው ጥበብና ችሎታ ያለው ሕዝብ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2015(ኤፍ ቢ ሲ) የሱዳን ሕዝብ አሁን ካጋጠመው ሁኔታ ለመውጣት የሚያስችለው ጥበብና ችሎታ ያለው ሕዝብ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሱዳንን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት÷የጎረቤት አገር ሱዳን ህዝቦች ከጥንትም ጀምረው ነፃነታቸውን የሚወዱ እና ብሄራዊ ክብራቸውን  አስጠብቀው የቆዩ ህዝቦች መሆናቸው አውስተዋል፡፡

የሱዳን ህዝብ ከሚወሳባቸው አያሌ መልካም ባህሪያት መሀከል  ለጋስነት እና እንግዳ ተቀባይነታቸው ከምንም በላይ ጎልቶ ይጠቀሳልም ብለዋል።

እነዚህ እሴቶች ደግሞ ከማህበራዊ ትስስሩ በላይ የኢትዮጵያን እና የሱዳንን ህዝብ የሚያመሳስሉ እና ይበልጥ የሚያቆራኙ ብለውም ከሌላው እንዲለዩ ከሚያረጓቸው  እውነታዎች ሁነው እናገኛቸዋለን ነው ያሉት።

“እኛ ኢትዮጵያውያን ይህ ኩሩ የሱዳን ህዝብ አሁን ላይ እየገጠመው ያለውን ቀውስ በጥበብ ሊወጣው ይችላል ስንል ያለንን ፅኑ እምነት ለመግለፅ እንወዳለን” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የሱዳን ህዝብ የራሱን ችግር በራሱ እንዲፈታ መተው አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥  የማንኛውም የውጭ ጣልቃ ገብነት ዓላማም ሰላምን እና ድርድርን በተመለከተ ብቻ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ከዛ ውጭ በሆነ በማንኛውም ድብቅ አጀንዳ የተነሳሳ የጣልቃ ገብነት እንቅስቃሴ በታሪክ ሸንጎ ላይ ተጠያቂ የሚያደርግ ይሆናል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ በበኩሉ የሱዳን ህዝብ የውስጥ ችግሩን በለመደው ጥበባዊ አካሄድ በራሱ እንዲፈታ የሚመኝ እና የሱዳን ህዝብ ጥቅም ተከብሮ ማየት ትልቁ  ፍላጎቱ መሆኑንም በድጋሚ  አረጋግጠዋል፡፡

አሁንም በህገወጥ መልኩ በሀገሪቷ ውስጣዊ ችግሮች ወስጥ እጁን የሚሰድን  ማንኛውም የውጭ ሃይልን በፅኑ እንቃወማለን ሲሉም  አስገንዝበዋል።የረመዳን ወር የመጨረሻ ቀናት ሰላምና ፀጥታን ለማግኘት የሱዳን መፍትሄ እንደሚያገኝ ያለንን እምነት አስተላልፌአለሁ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.