Fana: At a Speed of Life!

ከጂቡቲ በድንበር አካባቢዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ የሚገቡ ዜጎችን ለመቆጣጠር እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከጂቡቲ በድንበር አካባቢዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡ ዜጎች ቁጥር ጨምሯል።

እነዚህ ዜጎች ተገቢው ቅድመ ምርመራ ሳይደረግላቸው እና በለይቶ ማቆያዎች ሳይሰነብቱ ወደ ህዝብ መቀላቀላቸው ደግሞ የከፋ ችግር እንዳያስከትል ስጋት ፈጥሯል።

ፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬት ከጂቡቲ ጋር የሚዋሰኑት የሱማሌ ክልል እንዲሁም የድሬዳዋ አስተዳደር በዘርፉ ምን እየሰሩ እንደሆነ ጠይቋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ፥ በድሬዳዋ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ ቫይረሱ የተስተዋለባቸው ግለሰቦች ጋር ንክኪ ለነበራቸው ስዎች ክትትል የማድረግ፣ እንዲሁም ስርጭቱን ለመቆጣጠር የሚረዱ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ በርከት ያሉ ዜጎች ከጂቡቲ ወደ ድሬዳዋ አስተዳደር መደበኛ ባልሆኑ መንገዶች አሁንም ድረስ እየገቡ መሆናቸው የቫይረሱ ስርጭት መቆጣጠር ስራ ላይ እንቅፋት ፈጥሯል።

የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ለምለም፥ መስል ችግሮች የኋላ ኋላ ሌላ መዘዝን ይዞ እንዳይመጣ ከማህበረሰቡ ጋር የጋራ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

የኮቪድ 19 ስርጭትን በመቆጣጠሩ ስራ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያለው የድሬዳዋ አስተዳደር ስላምና ጸጥታ ቢሮ አሁን ያሉ ስጋቶችን ይጋራል።

በአስተዳደሩ የሰላመና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙሳ ጠሃ፥ መደበኛ ባልሆነ ወይም ህገወጥ በሆነ መንገድ ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡ ስዎችን ለመቆጣጠር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ውስንነት እንዳለባቸው ያምናሉ።

መደበኛ ያልሆኑ ፍልሰቶችን ለመቆጣጠር ከአጎራባች ሶማሌ ክልል ጋር እየሰራን ነው ያሉት አቶ ሙሳ፥ የሚደረገው ጥረት ግን ክፍተቶች እንዳሉትም አልሸሸጉም።

ጉዳዮ የሚመለከተው ሌላኛው የሶማሌ ክልል በድንበር አካባቢዎች ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ከድሬዳዋ አስተዳደር እና ከፌደራል መንግስት ጋር የጋራ ስራዎች ስለመጀመራቸው ገልጿል።

የክልሉ ምክትል ርዕስ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ አሁን ላይ በድንበር አካባቢዎች ለይቶ ማቆያ ማእከላትን የማደራጀት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ነው ከፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ የገለጹት።

በአካባቢው ያሉ ችግሮች የፌደራል መንግስትን ድጋፍ የሚሹ በመሆናቸው አሁን ላይ የተጀመሩ ስራዎች እንዳሉ አቶ ሙስጠፌ መሃመድ ነግረውናል።

መደበኛ ባልሆኑ መንገዶች ከጂቡቲ ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡ ዜጎችን ለመቆጣጠር እና በአካባቢው አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ነው ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ የጠቆሙት።

በአወል አበራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.