Fana: At a Speed of Life!

የእንግሊዝኛ ቋንቋን በበጎ ፈቃደኝነት የሚያስተምሩ ዜጎች የሚመዘገቡበት ፖርታል ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርት ሚኒስቴር የእንግሊዝኛ ቋንቋን በበጎ ፈቃደኝነት የማስተማር ፍላጎት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የውጪ ሀገር ዜጎች የሚመዘገቡበት የመረጃ ፖርታል አልምቶ ሥራ አስጀመረ።

በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት የሚታየውን የጥራት ጉድለት ለማስተካከል በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ሌሎች የውጪ ሀገራት ዜጎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ ጥሪ ቀርቧል።

እንግሊዝኛ ቋንቋ የትምህርት፣ የሳይንስ፣ የምርምር፣ የአቬሽን እና ሌሎች መሠረታዊ ሁነቶች የሚከወኑበት በመሆኑ÷ በቋንቋው ያለን ክህሎት ማሳደግ የሚስተዋለውን የትምህርት ጥራት ጉድለት እንደሚያስተካክል ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፓለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ዓለም አቀፍ ተሰሚነት እና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ሚናው የጎላ ስለሆነ በዘርፉ ጠንክሮ መሥራት ይገባል ተብሏል፡፡

ለዚህም ሲባል በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት አሰጣጥ ዙሪያ የሚታየውን የጥራት መጓደል ለማሻሻል የተለያዩ አሠራሮችን ተግባራዊ እየተደረጉ ሲሆን÷ የትምህርት ሚኒስቴር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር ይፋ ያደረገው learn-english.moe.gov.et ነፃ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መማሪያ ዌብ ፓርታል አንዱ ማሳያ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የመምህራንን ብቃት የማሻሻል ሥራ ትኩረት የተሰጠው መሆኑ እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በሀገር ውስጥ እንግሊዝኛ የሚያስተምሩ መምህራን ልምድ እንዲያገኙ ዕድል ይፈጥል መባሉን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በተለይም በውጭ ሀገር ተወልደው ያደጉ ኢትዮጵያዊያን ዕድሉን እንዲጠቀሙበት ጥሪ ቀርቧል፡፡

ፖርታሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ለሆነ ማንኛውም አካል ምቹ የሆነ እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጡን የተመለከቱ መረጃዎች የተካተቱበት እንዲሁም የተሟላ ግንኙነት ለማድረግ የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የሚካሄደውን የመማር ማስተማር፣ ምርምር፣ ሥርዓተ ትምህርት እና ሌሎች ፕሮጀከት ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እገዛ ማድረግ የሚፈልጉ በጎ ፈቃደኛ ምሁራን እና የትምህርት ባለሙያዎች በ https://Ethernet.edu.et እንዲሁም በበጎ ፈቃደኝነት የእንግሊዘኛ ቋንቋን ለማስተማር ፍላጎቱ ያላቸው https://enhance-english.moe.gov.et ላይ ምዝገባ ማድረግ እንደሚችሉ ነው የተመላተው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.