Fana: At a Speed of Life!

የግብርናውን ዘርፍ በፋይናንስ በመደገፍ የተገኙ አበረታች ውጤቶችን ለማስቀጠል እየተሰራ ነው – አቶ አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርናውን ዘርፍ በፋይናንስ በመደገፍ እየተመዘገቡ ያሉ አበረታች ውጤቶችን ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ገለጹ።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴና ሌሎች የተቋሙ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በሳይንስ ሙዚየም የተጀመረውን የግብርና እና የሳይንስ አውደ ርዕይ  ጎብኝተዋል።

አቶ አሕመድ ሽዴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት÷ የግብርናውን ዘርፍ በፋይናንስ በመደገፍ አሁን እየተመዘገቡ የሚገኙ አበረታች ውጤቶችን ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ ነው።

የሀገሪቱን ልማት ለማረጋገጥ የግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠው በመግለጽ÷ ለዚህም የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።

በሰብልና በእንስሳት ኃብት ልማት፣ እንዲሁም በተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ላይ አመርቂ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

የግብርና ምርትና ምርታማነት በተለይም ደግሞ በስንዴ ምርት ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ነው የገለጹት፡፡

የግብርና ሚኒስትር  ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የኤግዚቢሽኑ ዓላማ የግብርና ዘርፉ ያለበትን ደረጃና እድገቱን ለሕዝቡ ማሳየት መሆኑን ጠቁመዋል።

ግብርናውን ለማዘመን የተጀመሩ ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋትና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ለዕይታ መቅረባቸውን ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.