Fana: At a Speed of Life!

አቶ ፍቃዱ ተሰማ በኦሮሚያ ክልል ሕዝቡ ለመከላከያ ሰራዊት ላሳየው ድጋፍ አመሰገኑ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ የክልሉ ሕዝብ ለመከላከያ ሰራዊት ላሳየው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

አቶ ፍቃዱ ባስተላለፉት መልዕክት÷ዛሬ በመላው ኦሮሚያ ሕዝቡ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያለውን ፍቅርና ክብር በሚመጥን መልኩ ድጋፉን አሳይቷል፤ጠንከር ያሉ መልዕክቶችንም አስተላልፏል ብለዋል።

መከላከያ የአንድነታችን ነፀብራቅ፣ የህልውናችን መተማመኛ፣ የክብራችን መገለጫ እና የሰላማችን ዘብ መሆኑ መላው ዓለም የሚያውቃው ደጋግሞም የመሰከረለት ሃቅ ነው ሲሉም አውስተዋል።

የክልሉ ሕዝብ መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ በፈለገባቸው ጊዜያት ሁሉ ልጆቹን መርቆ እስከመሸኘት ያለውን ጠንካራ ድጋፍ አሳይቷል ያሉት ሃላፊው÷ የሰራዊቱን ክብር በሚመጥን መልኩም ድጋፉን ቀጥሏል ብለዋል።

በመከላከያ ሰራዊት ላይ በጽንፈኛ ሃይሎች ከተለያየ አቅጣጫ እየተደረገ ያለውን የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደ ሕዝብ አጥብቀን የምንኮንነውና የምንጠየፈው አሳፋሪ ተግባር መሆኑን ሕዝቡ በድጋፍ ሰልፍ በይፋ አሳይቷል ነው ያሉት።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለሀገሩ ክብር ቀን ከሌት መከራን የሚቀበል በሱ መሞት ሚሊየኖችን የሚያኖር የቁርጥ ቀን ልጅ ነው ሲሉም አውስተዋል።

የክልሉ ሕዝብ አሁንም ሆነ ወደፊት ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያለውን ፅኑ ድጋፍ ያለምንም ማወላዳት አፅንቶ መቀጠልም እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

ዛሬ ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፋቸውን ላሳዩ የክልሉ ነዋሪዎች፣ አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የከተማ እና የገጠር ነዋሪዎችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

አቶ ፈቃዱ ለድጋፍ ሰልፉ ሽፋን ለሰጡ መገናኛ ብዙሃን እና ሁነቱ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ስራ ያከናወኑ የፀጥታ አካላትንም አመስግነዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.