Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ለኢንቨስተሮች ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የዲጂታል ሥርዓት ተዘርግቷል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል መዋዕለ ንዋያቸውን ለሚያፈሱ ባለሃብቶች ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የዲጂታል ሥርዓት መዘርጋቱን የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ይሄነው ዓለም፥ በአማራ ክልል በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ የሚያስችል እምቅ አቅም መኖሩን ተናግረዋል።

በክልሉ ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በ2015 በጀት ዓመት 483 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 4 ሺህ 724 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን በአብነት አንስተዋል።

ባለሃብቶቹ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ብረታ ብረት፣ በጨርቃ ጨርቅ በማኑፋክቸሪንግ እና ሌሎች ዘርፎች እንደሚሰማሩ አብራርተዋል።

አልሚዎቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡም ለ957 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል።

አልሚዎች ቀልጣፋ አገልግሎት ከአስፈላጊ መረጃ ጋር እንዲያገኙም ተደራሽ እና ዲጂታላይዝ አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።

በመሬት አቅርቦት፣ በመመሪያ እና ደንቦች እንዲሁም በኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መገምገሚያ መስፈርቶች ላይ ማሻሻያ መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡

የውጭ ባለሃብቶች፣ ዳያስፖራዎች እና የሀገር ውስጥ አልሚዎችም በክልሉ ባለው እምቅ ሃብት መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.