Fana: At a Speed of Life!

ቦምብ ለሸኔ የሽብር ቡድን ሊያቀብሉ ነበር ተብለው የተከሰሱ 2 ግለሰቦች በእስራት እንዲቀጡ ተወሰነ

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 50 የእጅ ቦምብ ለሸኔ የሽብር ቡድን ሊያቀብሉ ነበር ተብለው የተከሰሱ አማንኤል ግርማ እና አብዶ መላኩ በ3 ዓመት ከ7 ወራት እስራት እንዲቀጡ ተወሰነ።

የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ህገ መንግስታዊና በህገ መንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከተው ችሎት ነው።

ቀደም ሲል በክስ መዝገቡ ተካቶ የነበረ ደጋጋ ፈቀደ የተባለ 3ኛ ተከሳሽን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው መከላከሉን ገልጾ በነጻ ማሰናበቱ ይታወሳል።

የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ1996 የወጣዉን የወንጀል ህግ አንቀጽ 27 ንዑስ ቁጥር 1 እና አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ ና ለ እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 9/ሐ ስር የተደነገገውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት ባሳለፍነው 2015 ዓ.ም መጨረሻ በተከሳሾቹ ላይ ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

በክስ ዝርዝሩ ላይ እንደተመላከተው፤ ተከሳሾቹ የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ ቁጥር 10/2013 መሰረት ሽብርተኛ ብሎ የሰየመውን የሸኔ የሽብር ቡድንን በቀጥታ እየረዱ መሆኑን እያወቁ በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ከሚንቀሳቀሰው የሸኔ ሽብር ቡድን ታጣቂዎች ጋር ጥብቅ ግንኙነት በመፍጠር ለቡድኑ የተለያዩ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን፤ ተተኳሽ በማቅረብ እና ድጋፍ ማድረግ በተለይም በነሐሴ 6 ቀን በአ/አ ከተማ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ልዩ ቦታዉ ጋርመንት በሚባል ቦታ ከቀኑ 11፡30 አካባቢ 50 ኤፍ ዋን (F1) የእጅ ቦምብ ከ8 የቦምብ ፊዉዝ ጋር ማንነቱ ለጊዜዉ ካልተለየ ግለሰብ በመረከብና በነገታው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ወረዳ 14 ልዩ ስሙ ሰፈራ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በሚገኝ የ2ኛ ተከሳሽ መኖሪያ ቤት እያሉ ከነቦምቡ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል።

ዐቃቤ ሕግ ይህንን ጠቅሶ ሽብርተኛ ድርጅት የመርዳት ሙከራ ወንጀል ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

ተከሳሾቹ ክሱ ከደረሳቸው በኋላ የወንጀል ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው ክደው በመከራከራቸው ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ በክሱ ላይ የተጠቀሰው የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን በማረጋገጥ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

ተከሳሾቹ የመከላከያ ማስረጃ ያቀረቡ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ መርምሮ አንደኛና ሁለተኛ ተከሳሾች የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን ማስተባበል አለመቻላቸው ተገልጾ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።

በክስ መዝገቡ ተካቶ የነበረ 3ኛ ተከሳሽን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው መከላከሉን ገልጾ በነጻ አሰናብቶታል።

ከዚህም በኋላ ዐቃቤ ህግ ጥፋተኛ በተባሉ ተከሳሾች የወንጀል ድርጊቱን በቡድን በስምምነት የፈጸሙት መሆኑን ጠቅሶ በቅጣት ማክበጃነት እንዲያዝለት አስተያየት አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን አንድ የቅጣት ማክበጃ አስተያየትን እንዲሁም ተከሳሾቹ ያቀረቡትን 9 የቅጣት ማቅለያ አስተያየቶችን በመያዝ በመካከለኛ ደረጃ ሁለቱንም ተከሳሾች እያንዳንዳቸውን በ3 ዓመት ከ7 ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.