Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ ዘላቂ ሠላምን ለማጽናት የባለድርሻ አካላት ቅንጅትን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዘላቂና አዎንታዊ ሠላምን ለማጽናት የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

የክልሉ ፀጥታ ምክር ቤት የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸምና የቀጣይ 90 ቀናት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ከባለድርሻ ጋር በቦንጋ ከተማ መክሯል።

ምክር ቤቱ በዘጠኝ ወራት በተሰሩ ክልላዊ የሠላምና ፀጥታ ስራዎች እንዲሁም ሕገወጥነትን መከላከልና የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አኳያ የተሰሩ ተግባራትን በጥልቀት ገምግሟል።

በክልሉ የሚስተዋሉ የፀጥታ ስጋቶችን በመገምገም አፋጣኝ መፍተሔ ማስቀመጥ እንደሚገባ የተገለጸ ሲሆን÷ የተገኘውን አዎንታዊ ሠላም ለማጽናት የባለድርሻ አካላት ቅንጅት መጠናከር እንዳለበት ተጠቅሷል፡፡

የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት የፀጥታ መዋቅሮች ቅንጅት መጠናከር እንዳለበትም ምክር ቤቱ አሳስቧል፡፡

የሚከሰቱ ጥቃቅን ወንጀሎችም ማህበረሰባዊ መልክ እንዳይዙ በመከላከል ዘላቂ ሠላም ማስፈን ትኩረት እንደሚፈልግ ተጠቁሟል፡፡

በአርብቶ አደር አካባቢዎች ወንጀልን ለመከላከል በተሰጠው ትኩረት የፀጥታ አደረጃጀቶችን በማደራጀት እየተሰራ ነው መባሉንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።

ከጋምቤላ ክልል ጋር የጋራ ፎረም በማቋቋም በቅንጅት እየተሰራ ነው የተባለ ሲሆን÷ ይህም ከሌሎች ክልሎች ጋር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የጦር መሳሪያ ዝውውርና ህገወጥ ንግድን መከላከል ላይም እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡

ከደቡብ ሱዳን ጋር በሚያዋስነው ድንበር አካባቢ የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን ከሚመለከታቸው የፌዴራል አካላት ጋር በመሆን ለመፍታት እየተሰራ ነውም ተብሏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.