Fana: At a Speed of Life!

ሃይል ለማግኘት ለሚጠባበቁ 375 አምራች ኢንዱስትሪዎች ሃይል ለማቅረብ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በግብዓት አቅርቦት ችግር የኤሌክትሪክ ሃይል ለማግኘት ለሚጠባበቁ 375 አምራች ኢንዱስትሪዎች ሃይል ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

በአገልግሎቱ የሃይል አቅርቦት ማስተባበሪያ ሃላፊ አቶ ነብዩ በየነ÷ በአምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ የሚስተዋለውን የኤሌክትሪክ መቆራረጥ እና የሃይል እጥረት ችግር ለመቅረፍ በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

አሁን ላይም የአምራች ኢንዱስትሪዎች የታሪፍ መደብ ተጠቃሚ ደንበኞች የእርካታ ደረጃ 60 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱን ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በፈጠረው መነቃቃት አገልግሎቱ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት የቴክኒክ ኮሚቴ አቋቁሞ የሃይል አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ለአዳዲስ አምራች ኢንዱስትሪዎች ሃይል ለማቅረብ የወሰን ማስከበርና የግብዓት አቅርቦት ችግር ከፍተኛ ተግዳሮት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ከግብዓት እጥረት ጋር ተያይዞ ትራንስፎርመሮች እና ሌሎች የመስመር ዝርጋታ እቃዎች ከአቅማቸው በላይ የተሸከሙ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመፍታትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተከታታይ ምክክር እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በግብዓት አቅርቦት ችግር የኤሌክትሪክ ሃይል ለማግኘት ለሚጠባበቁ 375 አምራች ኢንዱስትሪዎች ሃይል ለማቅረብ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡም በኤሌክትሪክ መሰረት ልማት ላይ የሚደርስን ስርቆትና መሰል ጉዳቶች በጋራ እንዲከላከል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.