Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል በኮሮናቫይረስ የቤት ለቤት ልየታ 24 ነጥብ 6 ሚሊየን ሰዎችን ተደራሽ ማድረጉ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል በኮሮና ቫይረስ የቤት ለቤት ልየታ 24 ነጥብ 6 ሚሊየን ሰዎችን ተደራሽ ማድረጉን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለፀ።

የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳስታወቀው፥ በእስካሁኑ ልየታ 5 ነጥብ 7 ሚሊየን አባወራዎችን ማዳረስ ተችሏል።

በኢትዮጵያ በ2 ወር ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 272 የደረሰ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል ዜናውን እስካጠናከርንበት ጊዜ 17 ሰዎች የቫይረሱ ተጠቂ መሆናቸው ተነግሯል።

በኦሮሚያ ክልልም የቫይርሱ ስርጭት ያለበትን ደረጃ ለማወቅ እንዲያግዝ በቫይረሱ የተያዘው የመጀመሪያው ሰው በአዳማ ከተማ መገኘቱ ይፋ ከተደረገ ጀምሮ የቤት ለቤት ልየታው እየተከናው መሆኑ ነው የተገለጸው።

የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊ ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በክልሉ 21 ዞኖች እና 19 ከተሞች ልየታው የተከናወነባቸው ሲሆን፥ እስካሁንም 5 ነጥብ 7 ሚሊየን አባወራን ተደራሽ ማድረግ ሲቻል 24 ነጥብ 6 ሚሊየን ሰዎችም የልየታ ስራ ተከናውኖባቸዋል ነው ያሉት።

በቤት ለቤት ልየታው ምንም እንኳን ቫይረሱ ያለበትን ደረጃ በግልፅ ለማወቅ አስቸጋሪ ቢያደርገውም የቫይረሱ ምልክቶች ይሆናሉ ተብለው የታሰቡትን ማሳየት የጀመረ ሰው ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲሄድ እንደሚደረግም ነው የገለጹት።

ግለሰቡ ከሚሰጠው መረጃ በተጨማሪ የሙቀት መለኪያ መሳሪያን በመጠቀምም ሙቀቱ ቫይረሱ ያለበት ሰው ሊኖረው የሚችለው የሙቀት ደረጃ ላይ መሆን አለመሆኑም ይለያል።

በክልሉ በልየታው መሰል ትግባራትን በመከወን ተደራሽ ከተደረጉት ሰዎች ውስጥም 188 ሰዎች ተጠርጣሪ ሆነው መለየታቸውም ተመላክቷል።

ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 2 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው በምርመራ መረጋገጡን ዶክተር አብዱልቃድር ተናግረዋል።

ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የቤት ለቤት ልየታ አጋዥ ነው የሚሉት የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊ ዶክተር አብዱልቃድር፥ ልየታው ባይክናወን ሁለቱን ሰዎች ማግኘት አይቻለም፤ እነሱም ሊያስተላልፉ የሚችሉበት ሰውንም መገመት ይቻላል ነው ያሉት ።

ይህንም አጠናክሮ ለማስቀጠል 11 ሺህ 700 ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የተሰማሩ መሆኑን በመግለፅ፤ አንድ ጤና ኤክስቴንሽን በቀን 20 ቤት ተደራሽ ማድረግ እንድትችል የሚያስችል ስርዓት በመዘርጋት ክትትል እየተደረገ ይገኛልም ተብሏል።

አሁን ላይ በክልሉ ያለውን የሙቀት መለኪያ እጥረት በመቅረፍ በክልሉ እንደሚኖር የሚገመተውን 40 ሚሊየን ህዝብ ለማዳረስም ይስራል ነው የተባለው።

በሌላም በኩል የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር እስካሁን ድረስ 5 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፥ ከተማ አስተዳደሩም ቫይረሱን ለመከላከል እና ስርጭቱን ለመቀነስ የሚያስችል ስራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።

የቤት ለቤት ልየታ ላይም በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ነው የገለፀው።

በዚህም 100 ሺህ ቤቶችን በቤት ለቤት ልየታው መድረስ መቻሉን የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ አሳውቋል።

የከተማ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ በልየታው በከተማ እና በገጠር ከ30 እስከ 80 በመቶ የሚሆን ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

ይሁንና የልየታ ስራውን በስፋት ለማከናውን የሙቀት መለኪያ መሳሪያ እጥረት መግጠሙን የሚናገሩት ወይዘሮ ለምለም፥ በስራው ለሚሳተፉ የጤና ባለሙያዎች የሙቀት መለኪያ ተደራሽ እንዲሆኑ ለማድረግም ግዥ እየተፈፀመ መሆኑን ተናግረዋል።

በዙፋን ካሳሁን

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.