Fana: At a Speed of Life!

በበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት እስካሁን 800 ሺህ ሄክታር በዘር መሸፈኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ከታቀደው 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት እስካሁን 800 ሺህ ሄክታሩ በዘር መሸፈኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር ) ገለጹ።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) በበኩላቸው÷ የተሟላ የመስኖ አውታር ያለውና ዓመቱን ሙሉ የሚለማ መሬት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መድረሱን ተናግረዋል።

የመንግሥት የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተጀምሯል።

በግምግማው የመኸርና የመስኖ የግብርና ልማት እንቅስቃሴዎች የተዳሰሱ ሲሆን÷ በሩብ ዓመቱ በ17 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄከታር ላይ በዋና ዋና ሰብሎች ከለማው 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የደረሱ ሰብሎች ምርት መሰብሰቡ ተጠቅሷል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አምንቴ (ዶ/ር)÷ በተለይ ሰሞኑን ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በመኖሩ የደረሱ ሰብሎችን ምርት ሳይባክን በትብብር የመሰብሰብ ስራ በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን አንስተዋል።

በዚህ ዓመት 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴ በማልማትና 117 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት ወደ ስራ መገባቱን ጠቅሰው÷ በሩብ ዓመቱ 800 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን አብራርተዋል።

ለሚቀጥለው የበልግና መኸር እርሻ ዝግጅቶች እየተከናወኑ ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ የማዳበሪያና ሌሎች ግብዓቶች ግዥን በሚመለከት ካለፈው ዓመት ትምህርት በመውሰድ ከፍተኛ ሪፎርም መደረጉን ጠቅሰዋል።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) በበኩላቸው÷ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት እቅድ በግብርና የሚለማ መሬትና የውሃ እቅም መለየቱን ጠቅሰው÷ ኢትዮጵያ 10 ሚሊየን ሄክታር በተሟላ የመስኖ ልማት መልማት እንደሚችል መለየቱን ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥ የተሟላ የመስኖ አውታር ያለው መሬት በ2012 ከነበረበት 500 ሺህ ሄክታር በዚህ ዓመት ወደ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር ከፍ ማለቱን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

መጓተት የሚታይባቸው ትላልቅ የመስኖ ፕሮጀክቶች ላይ ያሉ ችግሮችን በመቅረፍ ሁሉን አቀፍና የተፋጠነ ስራ እየተከናወነ ሲሆን÷ ግድቦች በደረሱበት ደረጃ ወደ ልማት እንዲገቡም መታሰቡን አንስተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.