Fana: At a Speed of Life!

ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከማስታወቂያ ጋር በተያያዘ በአሜሪካ ክስ ተመሰረተበት

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ ፍትሕ ዲፓርትመንት በዓለማችን ትልቁ የገንዘብ ምንዛሬ ተቋም የሆነውን ቢናንስ ኩባንያ አስተዋውቋል በሚል በክርስቲያኖ ሮናልዶ ላይ ክስ መስርቷል፡፡

የቢናንስ ኩባንያ ምስረታውን በቻይና ያደረገ ሲሆን÷ የቻይና መንግስት የዲጂታል የገንዘብ ምንዛሬን መከልከሉን ተከትሎ ዋና መስሪያ ቤቱን ወደ ጃፓን በማዞር በዲጂታል ምንዛሬ በዓለማችን ቀዳሚ መሆን የቻለ ተቋም ነው፡፡

ኩባንያው በፈረንጆቹ 2021 በአሜሪካ የፍትሕ ዲፓርትመንት እና በአሜሪካ የውስጥ ገቢ አገልግሎት ተቋም ገንዘብ ማጭበርበር እና በታክስ ወንጀሎች ክስ ተመስረቶበት ቆይቷል።

በተመሳሳይ ዓመት ኩባንያው በእንግሊዝ  በገንዘብ ማጭበርበር፣ ያልተፈቀደ ገንዘብ በማስተላለፍ እና በማዕቀብ ጥሰቶች ክስ ተመሰርቶበት ከ4 ቢሊየን ዶላር በላይ የካሳ ገንዘብ ለመክፈል መስማማቱ የሚታወስ ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በ2022 የቢናንስ ኩባንያን ማስታወቂያ በመስራት የአሜሪካ ባለሃብቶች ለኪሳራ እንዲዳረጉ አድርጓል በሚል በአሜሪካ ክስ ቀርቦበታል፡፡

በክሱ ኩባንያው በክርስቲያኖ ሮናልዶ ስም “ሲ አር 7” የሚል ጽሑፍ የታተመባቸውን የዲጂታል ገንዘብ ስጦታዎችን ለደጋፊዎቹ ማበርከቱ ተመላክቷል፡፡

በዚህም ኩባንያው ከሮናልዶ ጋር በመሆን በአሜሪካ ባለሃብቶች ላይ የ1 ቢሊየን ዶላር ኪሳራ ማደረሱ ነው የተጠቆመው፡፡

ክርስቲያኖ ሮናልዶ በበኩሉ ÷”የዲጂታል ገንዝብ ስጦታ ያበረከትኩት ዓመቱን ሙሉ ከጎኔ ሆነው ላበረታቱኝ ደጋፊዎቼ እንጂ ለሁሉም ደጋፊዎች አይደለም፤ማስታወቂያም አልሰራሁም”  ሲል የቀረበበትን ክስ አስተባብሏል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሮናልዶ እና የቢናንስ ኩባንያ መልስ ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘ ታይምስ እና ቢቢሲ በዘገባቸው አስፍረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.