Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት ሦስት ወራት ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት 685 ሚሊየን ብር ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ሦስት ወራት 685 ሚሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት አስታወቀ።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዳጋቶ ኩምቤ እንደገለጹት÷ ገቢው የተሰበሰበው ከ411 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች አገልግሎት በመስጠት ነው፡፡

አገልግሎቱ የተቋሙን የአገልግሎት አሰጣጥና የክፍያ ሥርዓት ከኢትዮ-ቴሌኮምና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን ማድረግ መቻሉንም ገልፀዋል፡፡

በዚህም 293 ሺህ ጉዳዮችን በዲጂታል መተግበሪያ በማረጋገጥ እንደመዘገበ በመግለጽ የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውልና የብድር ውሎች ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ወራት 685 ሚሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን በመጥቀስም፥ በሩብ ዓመቱ የዕቅዱን 147 በመቶ ማሳካት መቻሉን አስረድተዋል፡፡

ከተገኘው ገቢ የመኪና ሽያጭና የባንክ ብድር ውል አብዛኛውን መጠን እንደሚይዝ አመላክተዋል።

ተቋሙ የሚሰጠው አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጠንም ሆነ በጥራት እያደገ መምጣቱን ተከትሎ የሚሰበሰበው የአገልግሎት ክፍያ መጨመሩንም ነው የተናገሩት፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት 2 ቢሊየን ብር ገቢ ከአገልግሎት ክፍያ ለማግኘት ዕቅድ እንደተያዘ መግለጻቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ዜጎች በሕጋዊ ውልና ማስረጃ መገልገል መጀመራቸው ለአፈጻጸሙ መጨመር ምክንያት መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.