Fana: At a Speed of Life!

ከቡና ወጪ ንግድ ከ571 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት ከቡና ወጪ ንግድ ከ571 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር ለፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬት እንዳሉት÷ከቡና ምርት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደገ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡

በተለይም የምርት ጥራትን ማሳደግ፣ የግብይት ሰንሰለቱን ማዘመንና የውጪ ምንዛሬ ማስገኘት ላይ በትኩረት መሰራቱን አንስተዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራትም ከ117 ሺህ 955 ቶን በላይ ቡና ወደ ተለያዩ የውጪ ሀገራት መላኩን ነው የተናገሩት፡፡

በዚህም 571 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ጠቁመው ÷በቀጣይ ገቢውን ይበልጥ ለማሳደግ በትብብር ይሰራል ብለዋል፡፡

ወደ ውጪ ከተላኩ የቡና አይነቶች ውስጥ ሲዳሞ፣ ነቀምቴ፣ ይርጋ ጨፌ እና ጅማ ቀዳሚ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

የቡና ምርቱ ዋና ዋና መዳረሻዎችም ሳውዲ ዓረቢያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ጃፓን እና ቻይና እንደነበሩ ጠቁመዋል፡፡

የዓለም ቡና ገበያ ዋጋ መቀዛቀዝ እና በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች የዘርፉ ተግዳሮቶች እንደሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.