Fana: At a Speed of Life!

በመስኖ መሬት ሽፋን የተገኘውን ስኬት በመስኖ መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ለመድገም ታቅዶ እየተሰራ ነው-አቶ ሽመልስ

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሉ በመስኖ መሬት ሽፋን የተገኘውን ስኬት በመስኖ መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ለመድገም ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ፡፡

ርእሰ መስተዳድሩ እስካሁን በተደረገ ጥናት በክልሉ ከዝናብ ጥገኝነት ውጭ በመስኖ ሊለማ የሚችል 6 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት መኖሩ መረጋገጡን አንስተው ተጨማሪ 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት ሊኖር እንደሚችልም ግምቶች እንደሚያሳዩ ገልፀዋል፡፡

ከአምስት አመታት በፊት ለሁሉም የመስኖ አይነቶች ጥቅም ላይ የዋለው አጠቃላይ መሬት ከ400 ሺህ ሄክታር በታች እንደነበርም ገልፀዋል፡፡

ሆኖም የበጋ ስንዴ ኢኒሼቲቫችን ተከትሎ በተደረገ እንቅስቃሴ፣ በመስኖ ስንዴ ብቻ ተጨማሪ 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት ወደመስኖ ልማት ማስገባት ተችሏል ብለዋል በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው፡፡

ከአምስት ዓመታት በፊት ከነበርንበት ደረጃ ጋር ሲነጻጸርም አጠቃላይ እድገቱ 900 በመቶ ነው፤ ይህ እድገት እንደ አስደናቂ የአፈፃፀም ስኬት ሊቆጠር ይችላል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በክልሉ “የአሥር ዓመት ዕቅድ” መሠረት አሁንም ሁለት የቤት ስራዎች ከፊታችን አሉ ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ አንደኛ ከአሁን በኋላም ወደ መስኖ ልማት ማስገባት የሚጠበቅብን ሰፊ መሬት አለ፤ ሁለተኛ ወደመስኖ ልማት የሚገባውን መሬት ከማስፋት ጎን ለጎን ዘላቂነት የሚሰጧቸውን የመስኖ መሠረተ ልማቶች ማሟላት ይጠበቅብናል ብለዋል።

እስካሁን ወደመስኖ ያስገባነው አብዛኛው መሬት እንደፓምፕ፣ ቦይ፣ ውሃ ሰበራና የመሳሰሉት ዘዴዎች ላይ የተንጠለጠለ ያሉ ሲሆን÷በመስኖ መሠረተ ልማት እስካልተደገፈ ድረስ ዘላቂ ሊሆን አይችልም ሲሉ ገልፀዋል።

እስካሁን መሰረተ ልማት ተሟልቶለት ወደዘላቂ የመስኖ ልማት የገባ መሬት ከ400 ሺህ ሄክታር አልዘለለም ነው ያሉት።

በዚህም የክልሉ መንግስት ይኸን በመረዳት በመስኖ መሬት ሽፋን የተገኘውን ስኬት በመስኖ መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ለመድገም አቅዶ እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በዚሁ መሠረት ለተጨማሪ 700 ሺህ ሄክታር መሬት፣ የቤተሰብ፣ የአነስተኛ፣ የመካከለኛና የከፍተኛ ደረጃ የመስኖ መሠረተ ልማት በማሟላት በአስር ዓመቱ እቅድ መጨረሻ ላይ የመስኖ መሠረተ ልማት ተሟልቶለት ወደዘላቂ የመስኖ ልማት የሚገባውን መሬት ከ1ሚሊየን ሄክታር በላይ የሚያደርሰው ይሆናል ነው ያሉት፡፡

ይህ ደግሞ የአገር አቀፉን የመስኖ ልማት ዕቅድ 82 ነጥብ 89 በመቶ የሚሸፍን እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.