Fana: At a Speed of Life!

በጊዜ የለንም መንፈስና በሰከነ አመራር ሰጪነት ወደ ተሻለ ሰላም እና ልማት እንሸጋገራለን – አቶ አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጊዜ የለንም መንፈስና በሰከነ አመራር ሰጪነት ህዝባችንን ከጎን አሰልፈን ወደ ተሻለ ሰላም እና ልማት እንሸጋገራለን ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባስተላለፉት ፥ ከህዝባችን ጋር የመከርንባቸው ውይይቶች ዘላቂ ሰላም እና ወንድማማችነትን የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል፡፡

ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማረጋገጥ በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ከተሞች ከህዝብ ጋር ምክክር መደረጉን ጠቅሰው ፥ በውይይቱ የፌደራልና የክልል አመራሮች የህዝቡን ፍላጎት ምንነት በአግባቡና በሰከነ መንገድ ማዳመጥ መቻላቸውን አንስተዋል፡፡

በዚህም በወንድማማችነት መንፈስ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ መድረስ መቻሉን ነው የጠቆሙት፡፡

“ካለንበት ችግር ለመውጣት ህዝባችን ዋነኛ የመፍትሔ ባለቤትና ተሳታፊ መሆን እንደሚገባ አሁንም በድጋሚ ለመጠየቅ እወዳለሁ” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል ፡-

ከህዝባችን ጋር የመከርንባቸው ውይይቶች ዘላቂ ሰላም እና ወንድማማችነትን የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን እና ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን ለማረጋገጥ በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ከተሞች ከህዝብ ጋር ምክክር ያደረግን ሲሆን ፥ በውይይቱ የፌደራል እና የክልል አመራሮች የህዝባችንን ፍላጎት ምንነት በአግባቡና በሰከነ መንገድ ማዳመጥ መቻላቸውን እናስታዉሳለን፡፡ በዚህም በወንድማማችነት መንፈስ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ መድረስ ተችሏል፡፡

ይህ ሁለንተናዊ ብልጽግናን አረጋግጠን የሀገራችንን መፃኢ እድል ለመወሰን ሁሉም እድሎች በእጃችን ላይ እንደሚገኙ ማሳያ ነዉ፡፡

በየመድረኮቹ የተነሱ ሃሳቦች ለመንግስትና ለፓርቲያችን በርካታ የውሳኔ ግብዓት ያገኘንባቸው ከመሆኑ ባሻገር የህዝባችንን የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የጋራ መግባባት የተደረሰበትና የአንድነት መንፈስ ያጠናከረ ነበር፡፡

በተለይም እነዚህ ዉይይቶች የአማራ ክልልን ህዝብ ጥያቄዎች ምን እንደሆኑ ከመገንዘብ አልፎ የሀገራችንን አንድነት ለማጽናት እና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ዕድል የሚሰጡ ሆነዉ አግኝቻቸዋለሁ፡፡

ክልሉ ዘርፈ ብዙ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመቶችን ከማስተናገዱ ባለፈ ለወደፊቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት መዘዝ ያስከተሉ ችግሮች መከሰታቸውን አሁንም የሚያሳዝን እና መሆን ያልነበረበት ክስተት ቢሆንም ይህንን ጊዜ ለመካስ በጊዜ የለንም መንፈስ በሰከነ አመራር ሰጭነት ህዝባችንን ከጎን አሰልፈን ወደተሻለ ሰላም እና ልማት እንሸጋገራለን፡፡

ካለንበት ችግር ለመውጣት ህዝባችን ዋነኛ የመፍትሔ ባለቤትና ተሳታፊ መሆን እንደሚገባ አሁንም በድጋሚ ለመጠየቅ እወዳለሁ፡፡

በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በውይይትና በድርድር መፍታት ምርጫ የሌለዉ ጉዳይ ሲሆን ፤ በተለይ በህብረተሰብ ዕድገት ውስጥ የሚታዩ ማናቸውም ዓይነት ጥያቄዎች የግድ በጦርነትና በግጭት መፍትሔ ያገኛሉ ተብሎ አይጠበቅምና፤ ይልቁንስ ከሁሉም በላይ ደግሞ ግጭትን እንደገቢ ማስገኛ ምንጭ እና አቋራጭ የመንግስት ስልጣን የመቆናጠጫ መንገድ የሚያደርጉ አካላት ድርጊታቸው ህዝብን ማሳነስና የማህበረሰቡን አንጡራ ሃብት ከማውደም ባሻገር ምንም ውጤት እንደማይኖረው ተገንዝበውና ቀልባቸውን ሰብስበው ጉዳዩን በማጤን ለሰላማዊ ትግል እራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸዉ፡፡

ክልላችን ያለበት የሰላም እጦት በእጅጉ የተሻሻለ ቢሆንም ፀረ ሰላም ሃይሎችን ለመጨረሻ ጊዜ የመቆጣጠር እና ፊታችንን ሙሉ በሙሉ ለሁሉም ነገር መሰረት ከሆነው የኢኮኖሚ ልማት ላይ ርብርብ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ የህግ የበላይነትን ከማስከበር በተጨማሪ አንፃራዊ ሰላም ባለባቸው የክልሉ አካባቢዎች መደበኛ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን ፥ በቅርቡም መደበኛ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚሰሩ ለማረጋገጥ እወዳለሁ፡፡

ህዝባዊ ውይይቶቹ በአጎራባች ክልሎችም የተካሄደ መሆኑ እና በተለያዩ ጊዜያት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመመለስ እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች መሆኑን ለመታዘብ የተቻለ ሲሆን ፥ እነዚህ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ሙሉ እምነት አለኝ ፡፡

የክልሉ መንግስት በሁለም ረገድ የሚያከናውናቸውን የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ሁሉም አካል በየደረጃው ሊደግፍ የሚገባ ሲሆን ፥ በዚህ ሂደት መላው የክልላችን ህዝብ፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የመንግስትና የፓርቲ አመራሮች እንዲሁም ልማት ወዳድ የሆናችሁ አጋር አካላት በሙሉ በክልሉ ውስጥ የሚካሄደውን የሰላም ማስከበር፣ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎችን በመተግበር ሂደት የበኩላችሁን አስተዋጽ እንድታበረክቱ ጥሪ አቀርባለሁ፡፡

በክልሉ የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቆጣጠር የፀረ ሰላም ኃይል ትግሉን አጠናክረን የምንቀጥል ሲሆን ፥ ለዚህ ተግባር ማህበረሰቡ ከፀጥታ ሃይሎች ጎን በመሰለፍ እያበረከተ ለሚገኘው አስተዋጽዖ ምስጋና ለማቅረብም እወዳለሁ፡፡ ይህን ቅንጅት የህዝባችንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በምንሰራውና የቅድሚያ ትኩረት በምንሰጠው የኢኮኖሚ ልማትም ንቅናቄ ስራ ሊቀጥል እንደሚገባ ለመጠቆም እፈልጋለሁ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.