Fana: At a Speed of Life!

የዓድዋ ድል በመላው የሀገራችን ህዝቦች የህይወት መስዋዕትነት የተገኘ ታላቅ ድል ነው-የሀረሪ ክልል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድል በመላው የሀገራችን ህዝቦች የህይወት መስዋዕትነት የተገኘ ታላቅ ድል ነው ሲል የሀረሪ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ገለፀ፡፡

ክልሉ 128ኛውን የዓድዋ ድል በዓል አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

ክልሉ ባስተላለፈው መልዕክትም÷ የአፍሪካ የነፃነት አርማ የሆነው የዓድዋ ድል በመላው የሀገራችን ህዝቦች የህይወት መስዋዕትነት የተገኘ ታላቅ ድል ነው መሆኑን አንስቷል።

ጀግኖች አባቶች በዓድዋ ጦርነት የውጭ ወራሪን በድል አድራጊነት ያሸነፉት በጀግንነታቸው፣ በአንድነታቸውና በዓላማ ጽናታቸው መሆኑን ገልጿል፡፡

ጀግኖች አባቶች የውጭ ወራሪን አሳፍረው በመመለስ የኢትዮጵያን ክብርና ነፃነት እንዳስጠበቁ ሁሉ የአሁኑ ትውልድም ህብረ ብሔራዊ አንድነቱን በማጠናከር ሀገርን ከድህነት ነፃ ለማውጣት በጽናት እንዲሰራ የክልሉ መንግሥት ጥሪ  አቅርቧል።

የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን ጽናትን፣ በዘመን የማይሸረሸር ጀግንነትን፣ ክብርን፣ ነፃነት፣ አንድነትንና መሰል ቱሩፋቶችን ያጸና ደማቅ ታሪክ መሆኑን የገለፀው ክልሉ  በመሆኑም የዓድዋን የድል በዓል ሲከበር በእኩልነት፣ በአብሮነት፣ በፍቅር እና በመተሳሰብ ሊሆን ይገባል ብሏል፡፡

በተጨማሪም በዓሉ ሲከበር ሀገራችን የጀመረችው የልማትና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታን በማጠናከር እንዲሁም እርስ በእርሳችን ያለንን አንድነት በማጎልበት አባቶቻችን ለዚህች ሀገር ሲሉ ለከፈሉት ዋጋ ክብር በመስጠት ሊሆን እንደሚገባም አሳስቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.