Fana: At a Speed of Life!

በዋና ዋና ማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፎች የተመዘገበው አፈጻጸም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ7 ነጥብ 9 በመቶ እንደሚያድግ አመላካች ነው ተባለ

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በዋና ዋና ማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፎች የተመዘገበው አፈጻጸም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ7 ነጥብ 9 በመቶ እንደሚያድግ አመላካች መሆኑ ተገለፀ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2016 የሁለተኛው ሩብ ዓመት የስራ አፈፃፀም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት ማካሄድ ጀምሯል።

በመድረኩም ያለፉት ስድስት ወራት የኢኮኖሚ ማህበራዊ እንዲሁም የፍትህና አስተዳደር ዘርፍ አፈጻጸም ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) የኢኮኖሚ ዘርፍ አፈጻጸምን ባቀረቡበት ወቅት ኢትዮጵያ በተያዘው በጀት ዓመት የ7 ነጥብ 9 በመቶ እድገት እንደሚመዘገብ ጠቅሰው፤ ባለፉት ስድስት ወራት በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፎች የተመዘገበው አፈጻጸም ይህን ያመላክታል ነው ብለዋል።

ለአብነትም በስድስት ወራት ከመኸር እርሻ ብቻ 496 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኘቱን ተናግረዋል፤በኢንዱስትሪ ዘርፍም የ10 በመቶ እድገት መመዝገቡን ነው ሚኒስትሯ የተናገሩት።

የወጪ ንግድ አፈጻጸምም የተሻለ ስኬት እያስመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለአብነትም ባለፉት ሰባት ወራት ከአገልግሎት ወጪ ንግድ ብቻ ከ4 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ መገኘቱን ተናግረዋል።

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ዘርፍም የተሻለ ስራ መከናወኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

የማህበራዊ ዘርፍ አፈጻጸም ሪፖርትን ያቀረቡት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ(ፕ/ር)÷ ባለፉት ስድስት ወራት በትምህርት፣ ጤና፣ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ እንዲሁም በባህልና ስፖርት ዘርፍ የተሻለ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ብቻ በስድስት ወራት ውስጥ ከ14 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻልና ተጨማሪ ትምህርት ቤቶችን መገንባት መቻሉን መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አቅመ ደካማ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የበጎ ፈቃድ ስራዎች በአገር አቀፍ ደረጃ በስፋት መከናወናቸውንም እንዲሁ።

በሌላ በኩል ባለፉት ስድስት ወራት የፍትህና አስተዳደር ስርዓቱን ለማሻሻል በርካታ የለውጥ ስራዎች መከናወናቸውን ያነሱት ደግሞ የፍትህና አስተዳደር ዘርፍ ሪፖርትን ያቀረቡት የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ(ዶ/ር) ናቸው።

በዘርፉ ከተከናወኑ ስራዎች መካከል በተለይ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ሰነድን አሳታፊ በሆነ አግባብ ማዘጋጀት መቻሉን ጠቅሰው፤ ሰነዱ በቀጣይ ጸድቆ ወደ ስራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

በስድስት ወራቱ በፌዴራልና በክልሎች በአጠቃላይ 168 የህግ ማርቀቅ ስራዎች መከናወናቸውንም በፍትህ ዘርፍ ከተከናወኑ ስራዎች መካከል መሆኑን ጠቅሰዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.